ለአካል ጉዳተኛ ሰራተኞች ትኩርት ሰጥቶ በኃላፊነት እየሰራ እንዳልሆነ ተጠቆመ

79
ሚያዝያ 16/2011 የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአካል ጉዳተኛ ሰራተኞች ትኩርት ሰጥቶ በኃላፊነት እየሰራ እንዳልሆነ ተጠቆመ ፡፡ የሚኒስቴሩ የስራ ሃላፊዎች ዛሬ የፌዴራል ዋና ኢዲተር ባወጣው የሦስት ዓመታት የክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ለመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የክዋኔ የኦዲት ግኝቱ ከ2007 እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ የተከናወነ ነው። የክዋኔ ኦዲቱ በሠራተኛ ማህበራት አደረጃጀትና መብት አጠበባቅ እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች በሚደረገው ድጋፍና ክትትል ላይ ትኩረት አድርጎ የተከናወነ ሲሆን፤ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ሚኒስቴሩ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት ልክ ስራውን በአግባቡ አለማከናወኑን አመላክቷል። ሚኒስቴሩ በመንግስትም ይሁን በግል ድርጅቶች ቅጥርና ምልመላ ወቅት አካል ጉዳተኞች እኩል ዕድል ማግኘታቸውን የሚያረጋግጥበት ስርዓት አለመዘርጋቱ በክዋኔ ኦዲቱ ተረጋግጧል። ሰራተኞች በማኅበር የመደራጀት መብታቸውን እንዳይጠቀሙ የሚከለክሉ አሰሪ ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ አለመውሰዱን በኦዲት ተረጋግጧል። በማኅበራት የተደራጁና ያልተደራጁ ሠራተኞች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ በቂ መረጃ በሚኒቴሩ ዘንድ እንደሌለ ታውቋል። ሠራተኞች ከማንኛውም አካል ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነውና ህጋዊ ጥበቃና ከለላ አግኝተው እንዲሠሩ ሚኒስቴሩ አገራዊ ሃላፊነቱን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሥራት አለመቻሉም በኦዲት ግኝቱ ተብራርቷል። ሚኒስቴሩ በውጭ አገሮች የሥራ ስምሪት የሠራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ መጠንን እንዲወሰን ያደረገውን ጥረት ያህል የአገር ውስጥ ሥራ ላይ ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን እንዲወሰን ትኩረት ሰጥቶ አለመሥራቱ ተገልጿል። የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱን ያቀረቡት ምክትል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ እንደተናገሩት፤ በአዲስ አበባ ብቻ በማኅበር ተደራጅተው መብትና ጥቅማቸውን ማስከበር የሚችሉ 7 ሺህ 614 ሠራተኞች ያሉ ቢኖሩም በማኅበር የተደራጁት ግን 514 ብቻ መሆናቸውን በክዋኔ ኦዲቱ ጊዜ መታዘባቸውን አስረድተዋል። ሚኒስቴሩ በቀጣይ አዲስ አበባና ድሬዳዋ መስተዳደርን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ያሉ በማህበር ሊደራጁ የሚችሉ ሠራተኞችን በመለየት በማኅበር እንዲደራጁ የማድረግ ሥራ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሃመድ የሱፍ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍንና የሰራተኞች የስራ ላይ ደህነነትና ጤንነት እንዲጠበቅና አካል ጉዳተኞች እኩል እድል እንዲያገኙ የማድረግ ሃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም። ሚኒስቴር ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ሠራተኞች ተደራጅተው ጥቅሞቻቸውን እንዲያስጠብቁ የሚያስችላቸው የመደራጀት መብታቸው ተግባራዊ አለመሆኑን ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ የብሔራዊ የሥራ ስምሪት ፖሊሲና ስትራቴጂ በማውጣት ለአገር ውስጥ ሠራተኞች የሚከፈለውን ዝቅተኛ የደመወዝ መጠንን ለማሻሻል  መሥራት እንሚጠበቅበትም አመልክተዋል። በፌዴራልም ሆነ በክልሎች በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚፈጸሙ ጥሰቶች ላይ ክትትል በማድረግ የማስተካከልና የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አቶ መሐመድ አሳስበዋል። በሁሉም ክልሎች ሰው ሰራሽ የአካል ጉዳተኞች መርጃ ማምረቻ ማዕከላት እንዲስፋፉ የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር ውጤታማ ሥራ መሥራት ከሚኒስቴሩ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል። የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታሁን አብዲሳ በሰጡት ምላሽ፤ ተቋማቸው የአሠራር፣ የአፈጻጸምና የአደረጃጀት ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ በክዋኔ ኦዲቱ የተመላከቱ ችግሮች በሙሉ ትክክል መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በተቋሙ ያለው አደረጃጀትም ተልዕኮን ለመወጣት የሚያስችል ባለመሆኑ አሠራሩን በመፈተሽ የተሻለ አደረጃጀት እንዲፈጠር እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል። በአገሪቷ ባሉ የኢንዱስትሪ አካባቢዎች ላይ የሠራተኞችን የሙያ ደህነነትና ጤነነት የሚከታተሉ ባለሙያዎች መመደባቸውንና በቀጣይም ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ብቻ የሚከታተል አደረጃጀትና መዋቅር እንዳልነበር ያስረዱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ችግሩን ለመፍታት ከወረዳ ጀምሮ ያሉ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ እንዲከታተሉ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ62 ዓመታት በፊት የተመሰረተ ነባር መስሪያ ቤት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም