የበልግ ዝናብ በአብዛኛዎቹ የአገሪቱ በልግ አብቃይ አካባቢዎች ይቀጥላል

56
አዲስ አበባ ሚያዝያ 16/2011 የበልግ ዝናብ በአብዛኛዎቹ የአገሪቱ በልግ አብቃይ አካባቢዎች በሚያዚያ ወር የመጨረሻዎቹ ቀናት ቀጣይነት ይኖረዋል ሲል የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ገለጸ። ከአመቺ የሚቲዎሮሎጂ ክስተቶች መጠናከር ጋር ተያይዞ ወቅታዊ ዝናብ ቀስ በቀስ በምስራቅና ምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ እየተስፋፋ ይሄዳልም ብሏል፡፡ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ከሞላ ጎደል ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና በተለይም የምድር ወገብን አቋርጦ ወደ አገሪቱ እንደሚገባ ከሚጠበቀው እርጥበት አዘል አየር ጋር ተያይዞ የተሻለ የደመናና የዝናብ ሥርጭት በደቡባዊው አጋማሽና በምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ እንደሚቀጥል የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በመጠንም ረገድ በአብዛኛው በአንዳንድ ሥፍራዎች ላይ ከባድ ዝናብ ሊያጋጥም እንደሚችል ይጠበቃል ብሏል ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ፡፡ በሚቀጥሉት 10 ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ የሸዋ ዞኖች፣ የምዕራብና የምሥራቅ ሐረርጌ፣ አርሲና ባሌ፣ ሶማሌ ክልል መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡ እንዲሁም የፋፈንና የሲቲ ዞኖች ሰሜናዊ ክፍል፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና ሀረሪ፣ ጋምቤላ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ዞኖች፣ ከአማራ ክልል የዋግህምራና የደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች፣ ከትግራይ ክልል የመካከለኛው፣ የምሥራቅና የደቡብ ዞኖች፣ የአፋር ዞን 1፣3 እና 5ም ተካትተዋል፡፡ እነዚሁ ዞኖች አልፎ አልፎ ከሚኖራቸው ጠንካራ የደመና ክምችቶች በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከባድ ዝናብ ይኖራል ነው ያለው ኤጀንሲው፡፡ በተጨማሪም ከምሥራቅ ጎጃም፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ የደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ ጋምቤላ፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳና የከማሺ ዞኖች፣ ጥቂት የደቡብ ሶማሌ ዞኖችና ቦረናና ጉጂ በአንዳንድ ሥፍራዎቻቸው ላይ በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል፡፡ የተቀሩት የአገሪቱ አካባቢዎች በአመዛኙ ደረቅ ሆነው ይቆያሉ ብሏል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም