ኢትዮጵያ የስፖርት ህግ ማዕቀፍ ያስፈልጋታል-የውይይቱ ተሳታፊዎች

101
አዲስ አበባ ሚያዝያ 16/2011 ኢትዮጵያ ራሱን የቻለ የስፖርት ህግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልጋት ተገለጸ:: የኢትዮጵያን ስፖርት አሁን ካለበት ደረጃ ለማሻሻልና እየተስተዋለ ያለውን የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ለመፍታት እንዲያስችል የስፖርት ህግ ማዕቀፍ ሊኖር እንደሚገባ ተገለጸ። የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር "የስፖርታዊ ጨዋነት ምንጮች" በሚል ርዕስ የሁለት ቀናት ውይይት አካሂደዋል። በዚህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ የወደፊት ስጋቶችና የመፍትሄ ሃሳቦችም ተነስተዋል። በተለይም የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች ከስታዲየም ኳስ ተመልካቹ ባሻገር ማህበረሰቡን ጉዳት ላይ እየጣለ መምጣቱ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ በስፋት ተነስቷል። የህግ ባለሙያው አቶ ሚሊዮን አለሙ፤ የኢትዮጵያ የስፖርት ህግ ተብሎ የወጣና በዝርዝር የተቀመጠ ነገር እንደሌላት ያብራራሉ። በተለይም እንደነ ግብጽ፣ ኬንያና ታንዛንያ ያሉ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሳይቀሩ ስፖርቱ እንዴት መደራጀት እንዳለበት ህግ አውጥተው በስራ ላይ በማዋል ከፍተኛ ሚና እንዳለቸውም ይገልጻሉ። የብሄር ጽንፈኝነት፣ የፌዴሬሽንና የክለቦች አደረጃጀት ችግር፣ የውድድር ፎርማት፣ ሙስና፣ የህግ የበላይነትን አለማክበር፣ የተሳሳተና ሃላፊነት የጎደለው የመረጃ ስርጭት አሁን ላይ ለስፖርታዊ ጨዋነት መደፍረስ እንደ ሁነኛ ምክንያቶች ተነስተዋል። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ሁሉ ሊፈታ የሚችል ራሱን የቻለ የስፖርት ህግ ማዕቀፍ ሊኖር እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የጸጥታ ችግር በስፋት በሚታይባቸው የክልል ጨዋታዎች ለረብሻ ምንጭ የሚሆኑ ችግሮችን በጥናት ለይተው መፍታት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ስታዲየሞች ለጸጥታ መደፍረስ ምክንያት እንዳይሆኑ ከተመልካች አቀማመጥ ጀምሮ አወቃቀራቸው ስርአት ሊኖረውና በቂ ግብአት ሊኖራቸው እንደሚገባም ተናግረዋል። በስታዲየም የሚመደቡ የጸጥታ አካላትም ስለ ስታዲየም አጠባበቅ በቂ ቅንዛቤ ሊኖራቸው ይገባልም ብለዋል። የአዲስ አበባና የፌዴራል ፖሊስ ኮሞሽኖች በበኩላቸው በጸጥታ ሃይሎች አማካኝነት ረብሻዎች እንዳይነሱና ችግሮችንም በተገቢው ሁኔታ እንዲፈቱ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ውይይቱ ለሁለት ቀናት የዘለቀ ሲሆን የተለያዩ የስፖርት ማህበራትና ፌዴሬሽኖች፣ ክለቦች፣ ደጋፊዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም