ከላሙ ወደብ ፕሮጀክት አንዱ የሆነው የመርከቦች ማቆያ በመጪው ሰኔ ወደስራ ይገባል

113
ሚያዝያ 16/2011 ከላሙ የወደብ ፕሮጀጀክት መካከል አንዱ የሆነው የመርከቦች ማቆያ ተርሚናል በመጪው ሰኔ ወደ ስራ እንደሚገባ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገለጸ:: የኢትዮጵያን የወደብ አማራጭ ለማስፋትና ከኬንያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር ከሚሰሩት ስራዎች መካከል አንዱ ከሆነው የላሙ የወደብ ፕሮጀክት አካል የሆኑት ሶስት የመርከብ ማቆያዎች ግንባታ ዝቅተኛው 62 ሲሆን ከፍተኛው 99 በመቶ ድረስ ተጠናቀዋል። በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የላሙ ወደብ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ደቡብ ሱዳንን የበለጠ ያስተሳስራል። ግንባታው 99 በመቶ የደረሰው አንደኛው የመርከብ ማቆያ ተርሚናል በመጪው ሰኔ ተመርቆ የላሙ ፕሮጀክት የሚጨበጥ ፕሮጀክት መሆኑን ማሳየት እንደሚቻል ተናግረዋል። የላሙ ወደብ ፕሮጀክት በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑን የተናገሩት አምባሳደር መለስ፤ የሁለቱ አገሮችን የንግድ ማህበረሰብ በማቀራረብ መስራት የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል። የላሙ ወደብ ፕሮጀክት ከወደብ ጋር ብቻ የተያያዘ እንዳልሆነ አምባሳደር መለስ ገልጸው የባቡርና የመንገድ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ በአገሮቹ መካከል ጠንካራ የየብስ ግንኙነትንም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያና ኬንያ ቪዛ ያለመጠቀምን ስምምነት ከተፈራረሙ ከ50 ዓመት በላይ እንዳለፋቸው ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ በተለይም ነጋዴዎች እንደፈለጉ ለመዘዋወር የሚያስችላቸው መሰረተ ልማት ሲያገኙ የተቀላጠፈ የንግድ ግንኙነት ለመዘርጋት እንደሚያስችል አብራርተዋል። ''ከላሙ ወደብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ የደረቅ ወደብ አገልግሎት የሚሰጥ ቦታም ተለይቷል'' ያሉት አምባሳደር መለስ፤ የኢትዮጵያ ሞያሌና የኬንያ ሞያሌን በማስተሳሰር አካባቢውን ትልቅ የገበያ መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል ተግባራት መጀመራቸውንም ጠቁመዋል። በሁለቱ መንግስታት በኩል ቁርጠኝነት በመኖሩ ከላሙ ጀምሮ እስከ ሞያሌ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ በኩል ከአዲስ አበባ እስከ ሞያሌ ድረስ ያሉ ከተሞች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል እንደሚኖር  ገልጸዋል። የባቡርና የመንገድ መሰረተ ልማት መስፋፋት በሰሜን ምስራቅ ኬንያና በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ያለውን ህብረተሰብ ህይወት እንደሚለውጥም ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ለረጅም ዓመታት በተረጋጋ ሁኔታ የቀጠለውን የኢትዮጵያና የኬንያ ፖለቲካዊ ዲፕሎማሲ ወደ ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ለማሸጋገር የሚያስችል ይሆናል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም