የኦህዴድ ቀጣይ የትግል አቅጣጫ የህብረተሰቡን ችግር መፍታት ነው--- የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል

52
ጅማ/ አምቦ/ነቀምቴ ሚያዝያ 24/2010 የኦህዴድ  ቀጣይ የትግል አቅጣጫ ህብረተሰቡ ባልረካባቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር መፍትሔ መስጠት መሆኑን የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሻፊ ዑመር ገለጹ። የጅማ ዞን እና የጅማ ከተማ አስተዳደር የአመራር አካላትን ያሳተፈ ስልጣና ትናንት ተጀምሯል፡፡ በጅማ ከተማ በተጀመረው የስልጠናው መክፈቻ ስነስርዓት ወቅት  የተገኙት የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴው  አባል እንደገለጹት ሀገሪቱ ባለፉት ተከታታይ  ዓመታት አለምን ያስደነቀ ዕድገት ብታመዘግብም የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ ህዝቡን  በከፍተኛ ሁኔታ በመጉዳቱ የፖለቲካ ቀውስ  እስከመፍጠር  የደረሰ ችግር አጋጥሞ ነበር፡፡ ከዚህም በመነሳት መንግስት የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል የሚያስችል  ጥልቅ ተሃድሶ በማካሔድ ክፍተቶችን ለይቶ ወደ መፍትሔ መሸጋገሩን ተናግረዋል። "የህዝብን አንድነት ለማጠናከር፣ በህገውጥ መልኩ የተያዙ መሬቶችን ወደ ህጋዊ አሰራር ለማስገባት ፣የኮንትሮባንድ ንግድ ለመቆጣጠር የተጀመሩ ስራዎች በጥንካሬ የሚነሱ ናቸው" ብለዋል ። ኦህዴድ የሚያካሄደው ቀጣይ የትግል አቅጣጫም  የህዝቡን  ፍላጎትና ጥያቄ መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሚሆን የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሻፊ አስታውቀዋል። የአመራር አካላት የተሳተፉበት የአምስት ቀናት ስልጠና በተመሳሳይ መልኩ  በምዕራብ ሸዋና በምስራቅ ወለጋ ዞኖች እየተካሄደ አንደሚገኝ ርፓርተሮቻችን  ከየስፍራው ዘግበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም