ነጻነትን… በሃላፊነት

365

በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)

ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ተፈጥሯዊ መብት ቢሆንም፤ የራስን ሐሳብ ለመግለጽ ሲባል በሌሎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል አገራት ህግ አውጥተውለት ሲሰሩበት ይስተዋላል። በአለም ላይ የመጀመሪያው ሀሳብን በነጻ የመግለጽና መረጃን በነጻ የማግኘት ድንጋጌ  የወጣው እኤአ 1766 በስዊዲን ምክር ቤት ነበር። ከዚያ ጊዜ አንስቶ አገራት እንደ አገራቸው ነባራዊ ሁኔታ እና አሰራር የፕሬስ ነጻነትን በህጋቸው በማካተት በተባበሩት መንግስታት ደረጃ ጊዜ ወጥቶለት በፈረንጆቹ አቆጣጠር ግንቦት መግቢያ ማክበር የጀመሩት። በመሆኑም በአገራችንም  በንጉሱ ዘመን ተሻሽሎ በ1948 ዓ.ም. በወጣው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 41 ላይ ‹‹ከመላው የንጉሠ ነገሥት ግዛት ውስጥ በሕግ መሠረት የንግግርና የጋዜጣ ነፃነት የተፈቀደ ነው፤›› በማለት ተደንግጎ ነበር፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥትም በ1980 ዓ.ም. የወጣው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 ላይ ኢትዮጵያዊያን የንግግር፣ የጽሑፍና የመሰብሰብ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ ደግሞ በ1987 ዓ.ም. በፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ላይ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሕጋዊ ዋስትና አግኝቶ ከሁለት አስርት አመታት በላይ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡

ይህንን ተከትሎ የቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ህግ በመነሳቱ የነጻ ፕሬስ መንፈስ እንዲቀሰቀስና ኢንዱስትሪውም ብዛት ያላቸው ተዋናዮችን እንዲያሳትፍ መሰረት ጥሏል። በወቅቱ ወደ ገበያው ብቅ ያሉ እንደ ጋዜጣና መጽሄት ያሉት የፕሬስ ውጤቶች ምንም እንኳን በአብዛኛው ሊባል በሚችል መልኩ በባለሙያ የሚሰሩ ባይሆኑም፤ ለአንባቢው ግን በምርጫ ቀርበውለት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ነገር ግን ሚዲያዎች የግልና የመንግስት በሚል በወጣላቸው ክፍል አጠቃላይ በሚያስተላልፉት ዘገባ ይዘቱንና አዝማመሚያውን የጨበጠና ከተልዕኮም አንጻር አካሄዳቸው አንድ ባለመሆኑ የሀሳብ መቧጨቅ እንዲመጣ ምክንያት ሆነ። በመሆኑም አንድም በሳል ባለሙያዎች ከገበያው መጥፋት፤ ሁለትም የግል ሚዲያዎች በገበያው ለመቆየት ባለመቻላቸው  ተገደው ከገበያ እንዳይወጡ በማሰብ የህዝቡን ቀልብ ለመሳብ በሚል ጽንፍ የያዘ ዘገባን ማሰራጨት ልማዳቸው አድርገው ቆይተዋል። በተቃራኒው በመንግስት የሚተዳደሩና ተጠሪነታቸውም የመንግስት የሆኑ መገናኛ ብዙሃን ነጻው ፕሬስ ኢ- ተዓማኒና በስሜት የሚነዳ፤ እንዲሁም በተዛባ መረጃ የህዝቡን ሰላም ለማደፍረስ የሚሰራ ተደርጎ መወቀሱ፤ በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ የፕሬስ ውጤቶች ከፕሮፓጋንዳ ስራ እና ከውሸት ሪፖርቶች የዘለለ የህዝቡን ድምጽ የመስማት አቅም የሌላቸው ተደርገው ተወስዷል።

ለዚህም ማሳያው በአንድ ወቅት ቲሞቲ ስፔንስ የተባለ በ1994 አስከ 1998 ድረስ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ትምህርት ያስተምር የነበረ ምሁር እንደሚናገረውም የኢትዮጵያ ፕሬስ በሁለት ጫፍ ተይዞ በአንባቢ ምርጫ የሚጎተትና የራሱን አጀንዳ መቅረጽ እንዳይችል ተጽዕኖ ውስጥ የወደቀ ፕሬስ እንዲሆን አድርጎታል።

ይህንንም ተከትሎ መንግስት በአዋጅ በመፈረጅ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንን እንደ አሸባሪ በመቁጠርና የሚዲያ ሀላፊዎችንና ጦማሪያንን በማሰር አገሪቷ ላለፉት 3 አመታት ቀውስ ስታስተናግድ ቆይታለች። ነገር ግን ብሶት የወለደው ህዝብ ፍላጎትና ትግል በመጣው አገራዊ ለውጥ ለተዘጉም ሚዲያዎችም ሆነ ለታሰሩ ጋዜጠኞች መፈታት ምክንያት ሆነ።

ዛሬ በኢትዮጵያ የህትመት ኢንዱስትሪ ውስጥ የግልና የመንግስት ጋዜጣና መጽሄቶች ተደምረው ቁጥራቸው ወደ 24 ባሽቆለቆለበት ሁኔታ፣ በተግባር ከ100 ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በብሄራዊ ቋንቋ የሚታተሙ የግል ጋዜጦች ቁጥር ወደ 3 በወረዱበት ሁኔታ፣ ብዛት ያላቸው በሃገሪቱ ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣትና ጤናማ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመዘርጋት አዳጋች እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።

በአገራችን ከ10 አመታት በላይ በቆየው ሚዲያዎችን የማፈን፤ ባለሙያዎችን የማሰር ብሎም የማሰደድ ተግባር መንግስት በህግም ሳይቀር ደንግጎ በመቆየቱ ምንም እንኳን ተግባሩ እና እየታየ ያለው የማፈን ስርዓቱ ከሚገመተው በላይ ቢሆንም ኢትዮጵያ ፕሬስ አፋኝ ሃገር መሆኗ ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ በተባለ ተቋም በ2018(እ.ኤ.አ) አለም አቀፉ የፕሬስ ፍሪደም ኢንዴክስ ላይ ከ180 ሃገራት ያገኘችው 150ኛ ደረጃ ነበር።  ነግር ግን በዚህ አመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ በመጣው አገራዊ ለውጥ በአገሪቷ የጋዜጠኞች መፈታትና ተዘግተው የነበሩ መጽሄቶች፣ ጋዜጦችና በአሸባሪነትም ተፈርጀው የነበሩትም ሚዲያዎች ነጻ በመሆናቸው  በዚህ አመት 40 ደረጃዎችን በማሻሻል 110ኛ መውጣቷ ለለውጡ ማሳያ ሆኖ ይወሰዳል። ይህም ተግባር አልጄዚራ በኢንሳይድ ስቶሪው ፕሮግራም እንዲሁም ሌሎች አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያንና ጋምቢያን በአስገራሚ ሁኔታ መሻሻል ያመጡ አገራት ናቸው በማለት እንደምሳሌ በማንሳት አድናቆት እየተቸራቸው ይገኛል።

ምንም እንኳን ለውጡን ተከትሎ የፕሬስ ነጻነቱ በመስፋቱ ሁሉም የመናገር ተፈጥሯዊ መብቱን መጠቀም ቢችልም፤ በአግባቡ መሆን እንደሚጠበቅበትም የሚናገሩ አልጠፉም። በመሆኑም ዛሬ የመጣውን ለውጥ በመጠቀም በዋናነት የተዘጋውን የመረጃ አማራጭ ወለል አድርጎ በከፈተው ነገር ግን በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ አደጋም ያለው ፌስቡክ በስፋት ጥቅም ላይ በመዋሉ ነው። በመሆኑም የመንግስትም ሆነ የግል ሚዲያዎች ይህንን ነጻነት በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባም አንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ለማ ያሳስባሉ። ሲቀጥሉም አሁን ነጻ ነው ተብሎ ያልተረጋገጠና በመረጃ ያልተደገፈ ጉዳይን ይዞ መውጣትና ማሰራጨት ህዝብንና መንግስትን ሆድ እና ጀርባ ከማረጉም በላይ የተጀመረውን ለውጥ አደጋ ላይ ይጥለዋል በማለት ያስረዳሉ።

በተጨማሪም መንግስት በሙያው ለተሰማሩ ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች ከአሁኑ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ወደፊት ለሚመጣው ችግር ከወዲሁ መፍትሄ እየተበጀለት መሄድ ይገበዋል ሲሉም ይገልጻሉ። ለዚህም ከመስሪያ ቦታ ጀምሮ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን እንዲያሟሉ በማድረግ አገራዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ በማድረግ፤ ከዚህ በፊት እንደ ችግር ሲነሳ የነበረውን የመንግስትና የግል ሚዲያ የሚለውን አሰራር ከወዲሁ ማስቀረት የግድ እንደሚል ታሪክ ያስተምረናል።  የኢትዮጵያ ፖለቲካም ዛሬ ይሆናል ተብሎ ባልተጠበቀ መስመር እየተጓዘ ያለው በዚሁ የታፈነ ድምጽ በፈጠረው ማዕበል እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።

መንግስት መረጃን እያረጋጋ እና ሚዛናዊነትን እያሰፋ በህግ የሚመራውን ፕሬስ ምህዳር እንዳይጠብ በመስራት ዛሬ የተረጋጋ የሚመስለው የፖለቲካ መስመር ዳግም እዚህም እዚያም በሚበታተኑ መረጃዎችና ባልተጠኑ ውሳኔዎች በማንኛውም ጊዜ ስላለመናወጡ ዋስትና የለም። በተጨማሪም የፕሬስ ነጻነቱ እንደ ተግዳሮት ከሚቆጠሩ ነገሮች በዋናነት ከነበረው ልማድ ያለመውጣትና አስፈላጊው መረጃ በመንግስት ሚዲያ በወቅቱ ያለመውጣት፣ የሚዲያ ካውንስል አለመኖር፣ በሚለቀቁ መረጃዎች አገራዊ ሀላፊነትን መዘንጋት፣ የዘርፉ ጠንካራ ባለሙያ አለመኖርና ሁሉም ጋዜጠኛ የመሆን “ሲቲዝን ጆርናሊዝም” ችግር የተሳሳቱ እና ያልጠሩ መረጃዎችን ፈጥኖ ማውጣት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በመሆኑም እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች እንደ መንግስት ቀድሞ በማሰብ ለሚመጣው ችግር ከወዲሁ ማረም ይገባል በማለት ጋዜጠኛ ጌታቸው ያስረዳሉ።

ሂውማን ራይትስ ዎች (HRW) ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵ በነፃነት የመሰብሰብና የመደራጀት መብት ከዚህ ቀደም እንኳን የሰብአዊ መብቱ ሊከበር ቀርቶ የደረሰውን ጉዳት ለመመርመር እንደማይፈቀድ ገልፆ በአብይ መንግስት ግን ቀሪ ጉዳዮች ቢኖሩም መሻሻል እንዳለ አመልክቷል።

በፕሬስ ነጻነት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን መሰረት ያደረገ ያለፈው አንድ አመት ሁኔታን ባለፈው አመት ሰኔ ወር ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት መረጃዎች ያለማንም ከልካይ በነፃነት እንዲሰራጩ የሚያስችሉ ተዘግተው የነበሩ የተለያዩ የጡመራ ብሎጎችን እና የዜና ድረገፆችን ጨምሮ 264 ዌብሳይቶች እንዲከፈቱ ማድረጉን አስታውሷል። በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩት ኢሳት እና ኦ ኤም ኤንን የመሳሰሉ የሚዲያ ተቋማት ክሱ ተነስቶላቸው ያለማንም ክልከላ ተግባራቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፤ ሲልም ሂውማን ራይትስ ዎች ያስረዳል።

በሃገሪቱ እስር ቤቶች ይገኙ የነበሩ ጋዜጠኞች በሙሉ ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉን እንደ መልካም  እርምጃ የወሰደው ዘገባው ይህም ከፈረንጆቹ 2004 ዓ.ም አንሰቶ የመጀመሪያው እንደሆነም አስፍሯል። በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ራሳቸው ከዚህ ቀደም አይነኬ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ዘገባዎቻቸውን እያሰራጩ እንደሚገኙ ያነሳው ሪፖርቱ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዘገባዎችን በየጊዜው እያቀረቡ እንደሆነም ጠቅሷል። ባለፉት አመታት ይፈፀሙ የነበሩ የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግሮች ላይ ያተኮሩ ዘጋቢ ፊልሞችን ሲያሰራጩ መታየቱን ሪፖርቱ አካቶ፤ ከዚህ ቀደም በእነዚሁ የመንግስት ሚዲያዎች ይቀርቡ የነበሩ ዘጋቢ ፊልሞች የሰብአዊ መብት ተጠቂውን መብት ለመንፈግ እንደነበርም አመልክቷል።

ስለሆነም የዳበረ ግብረገብነትና ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር ያላቸው ህዝቦች ባለቤት በሆነችው አገራችን ጋዜጠኝነትን በአግባቡ መጠቀም ያን ያህል አዳጋች አይሆንም፡፡ ሰውን ከሰው ጋር የሚያጋጭ ሰው በጠብአጫሪነት ይኮነናል፡፡ ማህበረሰባዊ ተቀባይነት ለማግኘት አለመዋሸት፣ ሰውን ማጋጨት ሳይሆን ማስታረቅ፣ ሳያጣሩ አለማውራትን መተዳደሪያ ደምብ ማድረግ የግድ እንደሆነም በብሮድካስት ባለስልጣን ህግና ደምብ ላይ በግልጽ ሰፍሯል፡፡

ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣ ቁጥር የሰው ልጅ ፍላጎትም አብሮ እያደገ መጥቷል፡፡ የሰው ልጅ ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ደግሞ መረጃ የማግኘት ፍላጎቱና ዝንባሌው መሆናቸውን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ለአንድ አገር ዕድገት ወሳኝ ሚና ካላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ መረጃ እንደሆነ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡

መንግስት የሃገሪቱን የሚዲያም ሆነ የኮምፒውተር ወንጀል ህጎችን በማሻሻል ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ዋስትና እንዲኖረው ሊያደርግ እንደሚገባ እና በበይነ መረብ እየተሰራጩ የሚገኙ የጥላቻ ንግግሮችን ለመግታት ተፈፃሚ ለመሆን የሚወጡ ህጎች ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን እንዳይጋፉ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ምሁራን ያስረዳሉ። ጋዜጠኞች ስራቸውን በነፃነት እንዲያከናውኑ መከታ ሊሆንላቸው የሚችል ህግ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ በመጠቆም፤ ከአዲስ አበባ ውጪ ለሚንቀሳቀሱ  ሚዲያዎች የህግ ሽፋን ሊደረግላቸው እንደሚገባም ምሁራኑ ያሳስባሉ።

በመሆኑም አለም አቀፉ የፕሬስ ነጻነት ቀን ዘንድሮ ለ26ኛ ጊዜ ከመጪው ሚያዚያ 23-25 2011 ዓ.ም ጀምሮ “መገናኛ ብዙሃን ለዴሞክራሲ፤ ለጋዜጠኝነትና ምርጫ በዘመነ የሃሰት መረጃ ስርጭት”  በሚል መሪ ቃልም ይከበራል። ለሶስት ቀናት የሚከበረው ይሂው ሁነት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት፣ በአፍሪካ ህብረት እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር  ነው መባሉን ከአዘጋጅ ኮሚቴው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

በአጠቃላይ የመንግስት ሚዲያዎች በአንድም በሌላም ጭልጥ ወዳለ አፍቃሬ መንግስት ተግባር እንዳይገቡና የህዝቡን ህይወት ረስተው የፓርቲ ፖለቲካ ማናፈሻ መድረኮች እንዳይሆኑ፤ በተቃራኒው የፕሬስ ነጻነቱን ዕድል ተጠቅመው በመስራት ላይ ላሉና ገና ወደፊት ለሚከፈቱት የግሉ ሚዲያም የመንግስት ሚዲያዎች በማይነኩት ችግሮችና ስህተቶች ላይ ብቻ አትኩሮ ተነባቢነትንና ተደማጭነት ለማግኘት ሲባል ብቻ ያልሆነ መረጃ እንዳያሰራጩ እና ችግሩ ሳይባባስ ሁለቱም ሚዲያዎች መረጃን በሀላፊነትና በሙያዊ ፍቅር እንዲያሰራጩ መድረኩ ሊመቻች ይገባል።