በሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡ ተከሳሾች ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተያዘ

62
ሚያዝያ  16//2011የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡ ተከሳሾች ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ያዘ። ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸዋል። በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት መስከረም 18 ቀን 2011 ዓ.ም ክሱን ያቀረበው ዓቃቤ ሕግ የቦምብ ጥቃቱ የተፈጸመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ለመግደል መሆኑን በክሱ አስታውቋል፡፡ በቦምብ ጥቃቱ ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች አቶ ጌቱ ግርማ፣ አቶ ብርሃኑ ጃፋር፣ አቶ ጥላሁን ጌታቸው፣ አቶ ባህሩ ቶሎሳና አቶ ደሳለኝ ተስፋዬ ናቸው፡፡ በዛሬው እለት ፍርድ ቤት የቀረቡት እነዚሁ ተከሳሾች ''እጃችን ከተያዘበት አንስቶ ወደ 10 ወራት ገደማ ይጠጋናል፤ ፍርድ ቤቱ የፍርድ ሒደቱን በፍጥነት ጨርሶ የተፋጠነ ፍትሕ እንድናገኝ ያድርግ '' በማለት ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱ በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ተደራራቢ የክስ መዝገብ በመኖራቸውና የእያንዳንዱንም መዝገብ ምስክር መስማትና ሌሎች የፍርድ ሒደቶችን በማካሔድ ላይ መሆኑን ገልጿል። በተቻለ መጠንም ይሕንን ተግባራት በማጠናቀቅ ተከሳሾች ተገቢውን ፍትሕ እንዲያገኙ እየሰራን ነው በማለትም ይገልጻል። በመጨረሻም በተከሳሾቹ መዝገብ ላይ ቀረኝ የሚለውን የምርመራ ስራ በማጠናቀቅና ብይን ለመስጠትም ለግንቦት 15 ቀን 2011ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም