ኢትዮጵያና ቻይና የኢንቨስትመንት ስምምነት አደረጉ

102
አዲስ አበባ ሚያዚያ 16/2011 ኢትዮጵያና ቻይና 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ስምምነት አደረጉ። ቻይና እስከ ፈረንጆች 2018 መጨረሻ ድረስ ኢትዮጵያ የወሰደችውን የብድር ወለድ ሙሉ በሙሉ ሰርዛለች። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቻይና የቤልት ኤንድ ሮድ ጉባኤ ለማሳተፍ ከአንድ ቀን በፊት ቤጂንግ መግባታቸው ይታወሳል። ከጉባኤው በፊትም ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን ቻይና የኢትዮጵያን የተጠራቀመ የብድር ወለድ የሰረዘች ሲሆን የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክትን እንደምትደግፍ አስታውቃለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የስትራቴጂ አጋርነት አጠናክራ መቀጠል እንደምትሻ አስረድተዋል። የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ተሳታፊ የሆነችበት የቤልት ኤንድ ሮድ ማእቀፍ ቀዳሚ ውጤት መሆኑን አስታውሰው፤ በቻይና እስር ላይ የምትገኘው ኢንጂነር ናዝራዊት አበራ ጉዳይ እንዳሳሰባቸውም ገልፀዋል። ከዚህ ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከቻይናው የስቴት ግሪድ ኩባንያ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ የኢንቨስትመንት ስምምነት ተፈርሟል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ስምምነቱ በዋናነት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ኃይል አቅርቦት፣ ለሁለተኛው የአዲስ ጂቡቲ የባቡር መሥመርና በከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማዳረስ የሚያስችል ነው። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሲኖሹር ከተባለው የቻይና የውጪ ንግድና የብድር ኢንሹራንስ ኩባንያ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱም የኩባንያው ኃላፊዎች ለኃይል ማመንጫ ለተገባው የኢንቨስትመንት ስምምነት ትግበራ ሙሉ ትብብር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም