የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን ማካሄድ ጀመረ

59
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010  የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዛሬ መደበኛ ስብሰባውን ጀምሯል። የኢህአዴግ  ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጸው፤ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የሁለት ዓመት ተኩል አፈፃፀምን በጥልቀት ይገመግማል። ኮሚቴው የእቅዱን አፈጻጸም ግምገማ ከተመለከተ በኋላም ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ወር የመጀመሪያ ሳምንታት  የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመካከለኛ ዘመን አፈፃፀም አስመልከቶ ከተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ማድረጉ ይታወሳል። በውይይቱ ላይም መሰረተ ልማቶችን አቀናጅቶ ተግባራዊ አለማድረግና የገበያ ትስስር አለመፍጠር በእቅድ ዘመኑ ቀዳሚ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ተጠቅሰዋል። የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ስብሰባ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ መሆኑን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም