ኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል እንሰራለን..በምዕራብ ሸዋ ዞን የካቢኔ አባላትና ሠራተኞች

107
አምቦ ግንቦት 27/2010 የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርና አስተሳሰብን በመዋጋት የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል እንደሚሰሩ በምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኙ  የካቢኔ አባላትና የኦህዴድ አባል የመንግስት ሠራተኞች ገለጹ፡፡ የካቢኔ አባላትና ሠራተኞቹ የተገኙበት ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ዛሬ በአምቦ ከተማ ተካሂዷል፡፡ ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ሰለሞን መንግስቱ "ለህብረተሰቡ የቅሬታ ምንጭ የሆነውን ኪራይ ሰብሳቢነት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት የኦህዴድ አባላት ጠንክረን ልንሰራ ይገባል" ብለዋል። በጥልቅ ተሀድሶ ወቅት ከተለዩ በርካታ ችግሮች መካከል የተወሰኑትን መፍታት ቢቻልም በተለይ ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዘው የተነሱ ችግሮችን በመፍታት በኩል አሁንም ውስንነት አንዳለ ገልጸዋል፡፡ በሕብረተሰቡ የተነሱ ቅሬታዎችን መፍታትም ሆነ በልማት ሥራ ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው ሰላም ሲረጋገጥ በመሆኑ በቀጣይ በአካባቢያቸው የሰፈነውን ሰላም ለማስቀጠል ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የኖኖ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጉደታ ደስታ በበኩላቸው በወረዳቸው ስር የሰደደ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ድርጊት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ ድርጊቱ ሕብረተሰቡን ለምሬት የሚዳርግ ከመሆኑ ባለፈ የኦህዴድ እንቅስቃሴን የሚገታ በመሆኑ እንደሚታገሉት ተናግረዋል፡፡ የዞኑ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ዘውዴ ደስታ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በጥልቅ ተሀድሶው እየተመዘገበ ያለው ውጤትና እየታየ ያለው ለውጥ ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ መጀመሩን ገልጸዋል። "ይህን ለማጠናከር ሰላም ወሳኝ በመሆኑ በተለይ አመራር አካላትና በየደረጃው ያሉ መዋቅሮች በቁርጠኝነት መስራት ይገባናል" ብለዋል። ጥልቅ ተሀድሶን ተከትሎ በአገልግሎት አሰጣጥና በመልካም አስተዳደር መስኮች እየተመዘገቡ ያሉ አበረታች ውጤቶችን አመራሩ በማስቀጠል ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ማረጋገጥ እንዳለበት የገለጹት ደግሞ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አብዱላዚዝ መሀመድ ናቸው። ደርጅቱ ባለፉት ዓመታት ባደረገው ትግል ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውንና በክልሉ ሰላም መስፈኑን ጠቁመዋል። በቀጣይም በየደረጃው ያለው አመራረር ከኪራይ ሰብሳቢነት ነጻ በመሆን የአካባቢውን ብሎም የክልሉን ሰላም ጠብቆ ለማቆየት መስራት እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት፡፡ "በተሰማራንበት የሥራ ዘርፍ ቀንና ሌሊት በሀቀኝነት መስራት የሁላችንም ድርሻ ነው" ሲሉም ገልጸዋል። የምዕራብ ሸዋ ዞን ኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገዛህኝ ከበደ  "በሃይማኖት፣ በብሔርና በአካባቢነት መከፋፈል የህዝብና የአገር ደህንነትን የሚያፈራርስ በመሆኑ አጥብቀን ልንዋጋ ይገባል" ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል በተደረገው ድርጅታዊ ግምገማ 14 የዞን እንዲሁም 173 የወረዳ አመራሮች ከስልጣን እንዲወርዱ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ባወጡት ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የሃይማኖት አክራሪነት፣ ዘረኝነትንና አካባቢነትን በቁርጠኝነት እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል። መድረኩ ጥልቅ ተሀድሶን ተከትሎ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን በማስቀጠል የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመራሩ በትጋትና በቁርጠኝነት እንዲሰራ የማነሳሳት ዓላማ እንዳለው ተመልክቷል። በኮንፈረንሱ ላይ ከ700 በላይ የወረዳና የዞን አመራሮች እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም