የህዝቡን አንድነት በማጠናከር የበለጸገች ኦሮሚያን ለመገንባት እንደሚሰራ የክልሉ መንግስት ገለጸ

51
ሚያዚያ 15/2011የህዝቡን አንድነት በማጠናከር በልማት የበለጸገች ኦሮሚያን ለመገንባት ሌት ተቀን እንደሚሰራ የክልሉ መንግስት ገለጸ። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የአቋም መግለጫ አውጥቷል። ቢሮው በላከው መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው የክልሉ መንግስት በሚያከናውናቸው ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ፣ የክልሉን ህዝብ ጥያቄ ለመመለስ በሚያስችል መልኩ ተይዟል፤ ትላልቅ ውጤቶችም ተመዝግቧል። በተሰሩ ሥራዎችም የክልሉ ህዝብ ያደረጋቸው ድጋፎች፣ ትችቶችና ስህተት ባለባቸው ጉዳዮች ላይም አመራሩ እንዲስተካከልና በማንኛውም ችግር ወቅት ከጎኑ በመቆሙ የክልሉ መንግስት ክብርና ምስጋና አለው ብለዋል። ዛሬም መንግስት ለህዝቡ ባለው አክብሮት በቀጣዮቹ  ተግባራት ውስጥ ህዝቡን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። አሁን ያለውን ነጻነት ያስገኘው የኦሮሞ ህዝብ በአንድነት መቆም በመጀመሩ መሆኑንም መግለጫው አስፍሯል። የኦሮሚያን አንድነት የሚያጠናክረው አሸናፊ ሐሳብና ጠንካራ አመራር ነው ያለው መግለጫው  የህዝቡን አንድነት የበለጠ ለማጠናከርና ለበለጠ ስኬት እንደሚሰራም ተገልጿል። ለኦሮሞ ማንነት፣ ለኦሮሚኛ ቋንቋ ና ወግ እድገት በተሟላ መልኩ ይሰራል ያለው መግለጫው፤ ትላንት በነበረው ተንኮልና ደባ የክልሉ ሰላም መደፍረሱንና የልማት ሥራ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይሰራ እንቅፋት መሆኑ ተገልጿል። ኦሮሚያ የሚለማው፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚሻሻለው ሰላም ካለ ብቻ በመሆኑ  ሰላምና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው ለኦሮሞና ኦሮሚያ ዋስትና የሚሆን የሰላም ሃይልን የማደራጀት፣ የመደገፍና የማጠናከር ሥራ ይሰራል ብሏል። ለውጡን ለማስቀጠልና  ጠንካራ ኢትዮጵያን  መገንባት  የሚቻለው ጠንካራ ኦሮሚያን ከገነባን ብቻ ነው ያለው መግለጫው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል  በተሰማራበት የሥራ መስክ  ኦሮሚያን ከመሰረቱ ለመቀየር መሆኑን ተረድቶ ሌት ከቀን ሊሰራ ይገባል ነው የተባለው። ያለውን ሃብት ለኢኮኖሚ እድገት በመጠቀም የህዝቡን አኗኗር ለመቀየር  እንሰራለን ያለው መግለጫው፤  ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሚያስችሉ እድሎችን በመለየት፣ በማቀድና ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋት  የኢኮኖሚ ምንጭ መፍጠር እንደሚገባም ተጠቁሟል። ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ የተማረ የሰው ሃይል ማፍራት፣ ጤናማ ህብረተሰብ ለመፍጠር የመድሃኒት አቅርቦት እንዲሻሻል፣ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት እንዲፋጠንና የፕሮጀክቶች አፈጻጸም እንዲሻሻል በቅንጅት ይሰራል ብሏል መግለጫው። አሁን የተደረሰበት ምዕራፍ ቄሮዎችና ቀሬዎች በከፈሉት መስዋዕትነት ነው ያለው መግለጫው፤ በማንኛውም መንግስት በሚያከናውናቸው ሥራዎች ውስጥ የወጣቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑም ተጠቁሟል። የክልሉ መንግስት የቀጣይ  ትኩረት የሚሆነው ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሆነም  የጠቀሰው መግለጫው ማንኛውም በክልሉ የሚካሄድ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ለወጣቶች የሥራ እንዲል የሚፈጠርበት ይሆናል ብሏል። የክልሉን ልማትና  የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን፤ የተጀመረውን  የኢኮኖሚ ንቅናቄ በማጠናከር ህዝቡ ያለውን ገንዘብ፣ የተፈጥሮ ሃብትና እውቀቱን አቀናጅቶ በመስራት ከድህነት ለመላቀቅ ይሰራል ብሏል መግለጫው። የወጣቶችን የሥራ እድል  ፈጠራ ጥያቄን ለመፍታትም በቅርብ ግዜ በጀት ተመድቦ ወደ ሥራ እንደሚገባም ተጠቅሷል። በተለያዩ ግዜያት በተሰራው ተንኮል  የክልሉ ህዝብ ያለውን  የአቃፊነት ወጉን በተጻረረ መልኩ ከተለያዩ አካባቢዎች ከሃብት ንብረታቸው የተፈናቀሉትን መልሶ ማቋቋም የክልሉ መንግስት ቁልፍ ተግባሩ አድርጎ ይዟል ብሏል መግለጫው። የልማት ሥራው በሚፈለገው ደረጃና የህዝቡን እርካታ እንዲያረጋገጥ በመንግስት አወቃቀር በተለያዩ ደረጃ የሚታዩትን ችግሮች በመለየት በድጋሚ በማጥራት መልሶ እንደሚደራጅም መግለጫው አረጋግጧል። የክልሉ መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥና ፍላጎትን ማርካት ነው ያለው መግለጫው ሊሰሩ የታቀዱ ሥራዎችን፣ የተከናወኑ ተግባራትን፣ የተፈጸመበት አግባብና  ቀጣይ እንዴት መከናወን እንዳለበት ከህዝቡ ጋር በቅርበት መወያየትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል። የክልሉ መንግስት  ህዝቡ የሰጠው ሃላፊነት  የኦሮሞና ኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ የሚገኙ ብሄር ብሔረሰቦች ጭምር በመሆኑ እንደ ሀገር አንድ ላይ መልማትና  አብሮ ማደግን ማዕከል ያደረገ ሃላፊነትን ዳር ለማድረስ እንደሚሰራም በመግለጫው ተጠቅሷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም