በሰቆጣ ከ14ሺህ 800 በላይ ሐሰተኛ የመቶ ብር ኖቶች ተያዙ

84
 ሚያዝያ 15/2011 በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሰቆጣ ከተማ 14ሺህ 800 ሃሰተኛ የመቶ ብር ኖቶች መያዛቸውን ፖሊስ  አስታወቀ፡፡ ኖቶቹ ለትንሳዔ በዓል ግብይት ጥቅም ላይ ሊውሉ የተዘጋጁ ነበሩ። የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል የሥራ ሂደት መሪ ረዳት ኢንስፔክተር ካሳሁን አየለ ለኢዜአ እንደገሉት ኖቶቹ የተያዙት ትናንት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ ነው። በከተማው 01 ቀበሌ ውስጥ የተያዙት ኖቶች የትንሳዔ በዓል ግብይትን ተጠቅሞ ጥቅም ላይ ለማዋል የተዘጋጁ እንደነበርም አስረድተዋል። ፖሊስ ከኅብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ባደረገው ክትትል ኖቶቹን መያዙንና ተጠርጣሪው ግን ለጊዜው ማምለጡን ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ የገበያ መሰል ወንጀል እንዳይፈጸም ኅብረተሰቡን እያስተማረ መሆኑንም ረዳት ኢንስፔክተር ካሳሁን ተናግረዋል፡፡ ኖቶቹ በገበያ አገልግሎት ቢውሉ ኖሮ፣ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ይፈጥር ነበር ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ከሚገበያዩ ነጋዴዎችና ጨለማን ተገን አድርጎ ከሚደረግ ግብይት እንዲቆጠብ አሳስበዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም