ዓለም ዓቀፍ ማህበረሰቡ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም የአካባቢው አገሮች የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ ይገባል-- ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ

48
አዲስ አበባ ግንቦት 27/2010 ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም በአካባቢው አገሮች የሚደረገውን የሰላም ጥረት መደገፍ እንደሚገባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አሳሰቡ። በኖርዌይ ጉብኝት ለማድረግ ኦስሎ የገቡት ዶክተር ወርቅነህ ከአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርክሰን ሶሪይዴ ጋር ባደረጉት ውይይት የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እውን እንዲሆን በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን/ኢጋድ/ እየተደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተ ገለጻ አድርጎላቸዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ከገጠማት ችግር በመውጣት ሰላምና መረጋገት እውን እንዲሆን እየተደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተም ገለጻ ማድረጋቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል። ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር፣ የመቻቻል ፖለቲካ እንዲዳብር እንዲሁም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መንግስት እያደረጋቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ትልቅ እርምጃ መሆናቸውንም ነው ዶክተር ወርቅነህ የገለጹት። የኖርዌዩ አቻቸው ኤርክሰን ሶሪይዴ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ጀምራለች" ብላ አገራቸው እንደምታምንና በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ዓለም በቅርበት እንደሚከታተል ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የሚካሄደው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤት እና ስኬት በአካባቢው አገሮች ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረውም ገልጸዋል። የኖርዌይ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸውም ነው ሚኒስትሯ የጠቆሙት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኦስሎ በረራ መጀመሩ የሁለቱን አገሮች የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንደሚያፋጥነውም አስረድተዋል። ኖርዌይ በስርዓተ ጾታ እና በአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ካለችው ኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንደምትሰራም መግለጻቸውን የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል። ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በኖርዌይ ቆይታቸው ከኖርዌይ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮችና መከላከያ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ከያራ ኢንተርናሽናል ስራ አስኪያጅ እንዲሁም ከኖርዌይ ቢዝነስ ልዑክ ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም