የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የዛሬ ውሎ በሰላም ተጠናቋል- የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ

115
አዲስ አበባ ግንቦት 27/2010 በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰጠ የሚገኘው የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና የመጀመሪያው ቀን ውሎ በተረጋጋ ሁኔታ መጠናቀቁን ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታወቀ። ከዛሬ ጀምሮ አስከ ሀሙስ በሚቆየው በዚህ ፈተና 284 ሺህ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን በመውሰድ ላይ ናቸው። በዛሬ ውሏቸውም የእንግሊዝኛና ሂሳብ ትምህርት ፈተናዎችን ተፈትነዋል። ለተማሪዎች ግንዛቤ ማስጨበጥን ጨምሮ ለፈተናው አስፈላጊው  ቅድመ ሁኔታ በመሟላቱ የዛሬው ፈተና በሰላም አንደተጠናቀቀ ኢዜአ ተዘዋውሮ የተመለከታቸው የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች ተናግረዋል። የኮከበ ፅባህ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ፈተና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ገብረመድህን አፅብሃ ተማሪዎቹ ተረጋግተው ፈተናቸውን ሲፈተኑ መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡ የየካቲት 12 መሰናዶ ትምህርት ቤት የፈተና ጣቢያ ኃላፊው አቶ አበባው ፀጋዬ እንዳሉት ደግሞ ተማሪዎቹ ገለጻ ተደርጎላቸውና በአግባቡም ተፈትሸው ወደ ፈተና በመግባታቸው ወጣ ያለ ነገር አልተከሰተም፡፡ የዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ፈተና ጣቢያ አስተባባሪው ተገኔ መንግስቱም አብዛኛው ተማሪ ከመኮረጅ ይልቅ በራሱ ጥረት ፈተናውን ሲሰራ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ገብረእግዚአብሄር ቀደም ብሎ አስፈላጊው ዝግጅት በመደረጉ "በዛሬው ውሎ ምንም አይነት ችግር አላጋጠመንም" ብለዋል። ከወትሮው በተሻለ መልኩ ሁሉም አካላት በባለቤትነት መስራታቸውም ለስኬቱ አስተዋፅኦ ማድረጉን ነው ያብራሩት። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር እስከ ፈተናው ፍፃሜ ሁሉም እንደ አስካሁኑ ኃላፊነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል። በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 993 የፈተና ጣቢያዎች በሚሰጠው ፈተና  የፀጥታ አካላትን ጨምሮ 16 ሺህ ባለሙያዎች እየተሳተፉ እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም