የወላይታ ድቻ እና የደቡብ ፖሊስ ጨዋታ በዝግ ሜዳ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄድ ተወሰነ

58
ሚያዝያ15 /2011 በ21ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በደጋፊዎች መካከል በነበረው ግጭት ምክንያት ያልተካሄደው የወላይታ ድቻ እና የደቡብ ፖሊስ ጨዋታ በዝግ ሜዳ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄድ ተወሰነ በ21ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በደጋፊዎች መካከል በነበረው ግጭት ምክንያት ያልተካሄደው የወላይታ ድቻ እና የደቡብ ፖሊስ ጨዋታ በዝግ ሜዳ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄድ ተወሰነ። ሚያዚያ 12 ቀን 2011 ዓ.ም በሐዋሳ ስታዲየም ወላይታ ድቻና ደቡብ ፖሊስ በ21ኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ከጨዋታው በፊት በሁለቱ ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ጨዋታው በማግስቱ 3 ሰዓት እንዲካሄድ ተወስኖ ነበር። የተፈጠረው ችግር ጨዋታውን ማካሄድ የሚያስችል ባለመሆኑ ጨዋታው ሳይካሄድ ለሌላ ጊዜ መራዘሙም አይዘነጋም። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት ያልተካሄደው የወላይታ ድቻ እና የደቡብ ፖሊስ ጨዋታ ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በዝግ ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል። በሌላ በኩል ሚያዚያ 13 ቀን 2011 ዓ.ም በሐዋሳ ስታዲየም ሐዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሊያድርጉት የነበረው ጨዋታ የሁለቱ ክለቦች የቅድመ ጨዋታ ስብስባ ላይ በከተማዋ ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ጨዋታው ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወቃል። የሊግ ኮሚቴው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከነገ በስቲያ በአሰላ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ እንዲደረግ ወስኗል። ታህሳስ 7 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሐዋሳ ከተማ ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም በሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሁለቱ ክለቦች በማግስቱ በዝግ ስታዲየም ጨዋታቸውን ለማድረግ የተገደዱ ሲሆን ጨዋታውም 0 ለ 0 በሆነ የአቻ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል። በወቅቱ በተፈጠረው ግጭትም ደጋፊዎች ተጎድተው በስታዲየም ውስጥ የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው እንደነበርም አይዘነጋም። የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር መስፍን ዴቢሶ የወላይታ ድቻ እና የደቡብ ፖሊስ እንዲሁም የሐዋሳ ከተማና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታዎች እንዳይካሄዱ ምክንያት ሆነዋል የተባሉ 37 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ትናንት ለኢዜአ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። የሃዋሳ ከተማ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ደስታ ዶጊሶ ፖሊስ ችግሩን ፈጥረዋል ብለው ከጠረጠራቸው ግለሰቦች በተጨማሪ ሌሎችንም አጋልጦ ለመስጠት እንዲያስችል በየክፍለ ከተማው ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ22ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ የቀን ለውጥ አድርጓል። በዚሁ መሰረት ሚያዚያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ሊደረጉ የነበሩ የ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሚያዚያ 22 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲካሄዱ የሊግ ኮሚቴው ወስኗል። በዚሁ መሰረት በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። በጅማ ስታዲየም ጅማ አባ ጅፋር ከሲዳማ ቡና፣ በሽረ ስታዲየም ስሑል ሽረ ከሐዋሳ ከተማ፣ በአዳማ አበበ በቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና፣ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባህርዳር ከተማ ከደቡብ ፖሊስ፣ በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከመከላከያ፣ በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከነማ ከድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ከደደቢት ጋር ይጫወታሉ። ሁሉም የክልል ጨዋታዎች የሚካሄዱት በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ነው። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ45 ነጥብ ሲመራ፣ ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ 37 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። መከላከያ፣ስሑል ሽረ እና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል በ13 ግቦች ሲመራ፣ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ12 የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በ11 ግቦች ይከተላሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም