በሀገሪቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ8ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ጥገና ተከናወነ።

95
አዳማ ሚያዚያ 15/2011 በሀገሪቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 870 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ ከ8ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ጥገና ማከናወኑ የመንገድ ፈንድ ኤጄንሲ ገለጸ። ኤጀንሲው የዘጠኝ ወር አፈፃፀምና የቀጣይ ቀሪ ጊዜያትን እቅድ ላይ ለመመክር ያዘጋጀው መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በዚህ ወቅት የመንገድ ፈንድ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ረሽድ ሙሐመድ እንዳሉ ከተከናወነው ጥገና ውስጥ በፌዴራልና በክልል መንግስት የሚተዳደሩ የአስፓልትና ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኝ የገጠር መንገድ ይገኙበታል። አፈጻጸሙ ከአቅዱ አንጻር  ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተው ይህም  ክልሎች የመንገድ ኤጄንሲዎችና የኢትዮዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሥራቸውን በእቅድ መምራት ባለመቻላቸው መሆኑን ገልጸዋል። ኦሮሚያ፣አማራ፣ደቡብና ትግራይ የተሻለ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ክልሎች መሆናቸውን አቶ ረሽድ አመልክተው የመስሪያ ቤታቸው 68 በመቶ ተጠቃሚ የሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን  ድርሻውን በተገቢው ባለመወጣቱ አፈጻጸሙ የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ ተናግረዋል። "በመድረኩ የእቅዱ ክንውን በመገምገም ቀጣይ የሥራ አፈፃፀሙን አሁን ካለበት ከፍ ለማድረግ የጋራ ርብርብ በማስፈለጉ ነው" ብለዋል። በኤጄንሲው የእቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አህመድ በባኩላቸው መስሪያ ቤታቸው ለመንገድ ጥገና የሚሆን ከነዳጅ የተጣለ ታሪፍ፣ ከተሽከርካሪ ፍቃድና ከሀገር አቋራጭ በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ካቀደው 2ቢሊዮን 600ሚሊዮን ብር ውስጥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2 ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል። ከሰበሰበው ገቢ 870 ሚሊዮን ብር ለመንገድ ጥገና ወጪ ማድረጉን ጠቅሰው " እስካሁን የበጀት አፈፃፀማችን 40 በመቶ ብቻ ነው "ብለዋል። የመንገድ ጥገናና እድሳት ሥራ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በሀገሪቷ ከሚገኙ 25 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የመንገድ ሀብቱ ያለበትን ችግርና ሁኔታ ለመለየት የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም አመልክተዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው የግምገማው መድረክ የመንገድ ዘርፍ ልማትን የሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ተወካዮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም