በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የእሳት ቃጠሎ በዱር እንስሳት ላይ ጉዳት አልደረሰም

143
ሚያዝያ 15/2011 በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተከሰተውን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ በዱር እንስሳት ላይ ጉዳት አለመድረሱን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የእሳት ቃጠሎውን ተከትሎ በዱር እንስሳት ላይ ጉዳት አለመድረሱን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በፓርኩ ብዝሃ ሕይወት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ በመጪው ክረምት በ25 ሄክታር የደን መሬት ላይ አገር በቀል ችግኞችን ለመትከል እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት ፓርኩ ቃጠሎውን ተከትሎ በባለሙያዎች ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት በፓርኩ ሁለት ጊዜ በተከሰተው የእሳት ቃጠሎ 1ሺህ 40 ሄክታር የተፈጥሮ ሀብት ቢጎዳም፤ በዱር እንስሳቱ ላይ ጉዳት አልደረሰም። ቃጠሎውን ተከትሎ ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ ባለሙያዎች ያካሄዱት ጥናት በፓርኩ ውስጥ በሚገኙ ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮና የምኒልክ ድኩላ ላይ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ ቀይ ቀበሮ ለምግብነት የሚያውላቸው አይጦችም በቃጠሎው ጉዳት ይደርስባቸዋል ተብሎ ሰፊ ግምት እንደነበር የተናገሩት ኃላፊው፣ እሳቱን መቆጣጠር ከተቻለ ወዲህ ግን በርካታ አይጦች እንዳልሞቱ  መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ በቃጠሎው ግጭ ከተባለው የመኖሪያ አካባቢያቸው ተሰደው የነበሩ በርካታ ቀይ ቀበሮዎችም ወደ ነባሩ መኖሪያቸው በመመለስ ምግብ ፍለጋ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ በቃጠሎው ጉዳት የደረሰበትን የፓርኩን ብዝሃ ህይወት መልሶ እንዲያገግም በመጪው ክረምት በ25 ሄክታር የደን ቦታ ከ15ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ለፓርኩ ሥነምህዳር ተስማሚ ናቸው የተባሉ ውጨና፣ አምጃ፣ ኮሶ፣ ወይራና የግራር ዛፍ አገር በቀል ዝርያዎችም ፓርኩ ባቋቋማቸው የችግኝ ጣቢያዎች በመፈላት ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ዝናብ መጣል ጀምሯል ያሉት አቶ አበባው፣ በሬዲዮ መገናኛ የታገዘ ጥብቅ የጥበቃ ሥርዓት በመዘርጋት በፓርኩ ስካውቶችና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ጥበቃ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት በተመዘገበው ፓርክ ከ900 በላይ ዋልያዎች፣ 120 ቀይ ቀበሮዎችና ከ7ሺህ በላይ ጭላዳ ዝንጀሮዎች እንደሚገኙ ከፓርኩ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በፓርኩ ዳግም ተቀስቅሶ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ የነበረውን የእሳት ቃጠሎ ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ረገድ የእስራኤል የእሳት ማጥፊያ ብርጌድ አባላትና የኬንያው ሄሊኮፕተር አብራሪ ርብርብ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም