በፓርኩ በአንድ ሳምንት 28 ጉማሬዎች ሞቱ

55
ሚያዝያ 15/2011 በጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ በአንድ ሳምንት ውስጥ 28 ጉማሬዎች መሞታቸውን የጉራጌ ዞን ህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ በጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ በአንድ ሳምንት ውስጥ 28 ጉማሬዎች መሞታቸውን የጉራጌ ዞን ህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ፈለቀ አባት ለኢዜአ እንደገለጹት ካለፈው እሁድ ጀምሮ በጉማሬዎቹ ላይ ለደረሰው የሞት አደጋ ምክንያት ማወቅ አልተቻለም ። የፓርኩ ጥበቃ ስካዎቶች በደረሳቸዉ ጥቆማ መሰረት ፓርኩን ለሚያስተዳደረው ለደቡብ ክልል አደጋውን ማሳወቃቸውን ተናግረዋል ። "ጉማሬዎች ቀን ቀን ውሃ ውሰጥ ይወላሉ ማታ ምግብ ፍላጋ ይወጣሉ" ያሉት አቶ ፈለቀ ፓርኩ የጥቅጥቅ ደን መገኛ እንደመሆኑ ደህንነቱ የተጠበቀ አለመሆኑን ጠቁመዋል ። በፓርኩ አካባቢ ያለው የህገወጥ ሰፈራ መበራከት ለአደጋው መንሰኤ ሊሆን ይችላል የሚል ግመት መኖሩን አመላክተዋል። "የአደጋውን ምንጭ ለማጣራት የፌዴራልና ክልል አመራሮችና ባለሙያዎች በስፈራው ተገኝተው የምርመራ ናሙና እየተወሰደ ነው" ብለዋል። በደቡብ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የዱር እንሰሳት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፍቃዱ ሺፈታ በበኩላቸው ሚያዝያ 11 ቀን 2011ዓ.ም. 24 የነበረው የሞቱ ጉማሬዎች ቁጥር ከሁለት ቀናት በኋላ 28 መድረሱን ተናግረዋል። "የተፈጠረው ችግር እንደ ሀገር የመጀመሪያ ነው ማለት ይቻላል" ያሉት አቶ ፍቃዱ በአካባቢው ህገወጥ የመሬት ወረራ እንዳለና አርሶአደሩ እርሻውን ለማስፋት ዛፎች እየተቆረጡ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡ እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ የተፈጠረውን ችግር በምርመራ በመለየት ጥቃቱ በሰዎች የደረሰ ከሆነ እርምጃ የሚወሰድበት ተፈጥሯዊ ከሆነም ጥንቃቄ የሚደረግባት ሂደት ለመፍጠር እየተሰራ ነው ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም