በአዳማ ከተማ የተፈጠረው አለመረጋጋት ወደ ነበረበት ሰላም መመለሱን ፖሊስ አስታወቀ

58
ሚያዝያ 14/2011 በአዳማ ከተማ በጫት ጫኝ አውራጅ ማህበራትና በዘርፉ በተሰማሩ ነጋዴዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ለማረጋጋት በተደረገው ጥረት ወደ ነበረበት ሰላም መመለሱን ፖሊስ አስታወቀ በአዳማ ከተማ በጫት ጫኝ አውራጅ ማህበራትና በዘርፉ በተሰማሩ ነጋዴዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ለማረጋጋት በተደረገው ጥረት ወደ ነበረበት ሰላም መመለሱን ፖሊስ አስታወቀ። የከተማዋ ፖሊሲ መምሪያ የህዝብ ግኑኝነት ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ዲኖ ይማም ለኢዜአ እንደገለጹት በአዳማ በተለምዶ ሃኒና አህመዴ በተባሉት አካባቢዎች በጫት ንግድ የተሰማሩ ማህበራት ወደ ህጋዊ የግብር ከፋይ መረብ እንዲገቡ ለማድረግ በአንድ የመሸጫ ማዕከል እንዲሰባሰቡ ይደረጋል። የተሰባሰቡትም በአስተዳደሩ  በኩል ሁኔታዎች ተመቻችቶ   ነው። በጫት ጫኝ  አውራጅ ማህበር የተደራጁ የከተማዋ ወጣቶች ደግሞ ጥቅማችን ይቀርብናል በማለት የንግዱ ማህበረሰብ ወደ ማዕከሉ ገብተው ግብይት እንዳይፈፀም በመከልከላቸው  ግጭት መፈጠሩን  ኮማንደር ዲኖ አመልክተዋል። ዛሬ  ከሰዓት በፊት የተፈጠረ ይሄው ግጭት የፀጥታ አካላት ፈጥነው በመድረስ ችግሩ እንዳይባባስ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በወጣቶችና  በጫት ጫኝ አውራጆች መካከል ችግሩ በመቀጠሉ በሰው አካል ላይ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ዝርፊያና ንብረት የማጥፋት ተግባር መፈፀሙንም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት የፌዴራልና የክልሉ ልዩ ኃይል የተፈጠረውን አለመግባባትና ግጭት ለመቆጣጠር ባደረጉት ጥረት መረጋጋትና ሰላሙም ወደነበረበት መመለሱን አስታውቀዋል። "በወጣቶች መካከል ወዥንብር በመፈጠር የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳካት የሚጥሩ ኃይሎች አይጠፉም " ያሉት ኮማንደር ዲኖ ፖሊስ በሰው አካል ላይ ጉዳት ያደረሱ፣በዝርፊያ የተሳተፉና የንብረት  ጥፋት የፈጸሙ ግለሰቦችን አጣርቶ ለህግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የከተማዋ ህብረተሰቡ እንደተለመደው ሁሉ ህገ ወጦችን ለማጋለጥ  ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም