የእንስሳት አረባብ ሥርዓቱ ወደ ዘመናዊነት የሚያሸጋግር የኤክስቴሽን አገልግሎት በመዘርጋት ላይ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

159
አዳማ ሚያዝያ 14/2011 አገሪቷ የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ የሚመጥን የአርሶና አርብቶ አደሩን የእንስሳት አረባብ ሥርዓት ወደ ዘመናዊነት የሚያሸጋግር የኤክስቴሽን አገልግሎት በመዘርጋት ላይ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። የእንስሳት ሀብት ልማት ዕርባታን ከልማዳዊ አሰራር ለማላቀቅበአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ስልጠና ዛሬ በአዳማ ተጀምሯል። የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገብረ እግዚአብሔር ገብረዮሓንስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የአገሪቱ የእንስሳት የአረባብ ሥርዓት ከልማዳዊነት ለማውጣትና ገበያ ተኮር የሚያደርግ አገልግሎት ለመዘርጋት እየተሰራ ነው። አገልግሎቱ የእንስሳት እርባታ ሥርዓቱ ልማዳዊና ቁጥርን ብቻ መሰረት ያደረገ ከሆነበት  መቀየር ዘርፉን በማልማት ፣በበሽታዎች መከላከል፣በመኖ ልማት፣በጥራትና በዝሪያዎች መሻሻል፣ አቅርቦት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል አስረድተዋል ። ይሁን እንጂ የገበያ መሠረተ ልማት አለመሟላት፣የግሉ ሴክተር ተሳትፎ አናሳ መሆን፣ለድንበር ዘለል በሽታዎች ተጋላጭ መሆን፣አየር ንበረት ለውጥ ተፅእኖን ተከትሎ የሚከሰት ድርቅና ተያያዥ ችግሮች ዘርፉን የሚፈታተኑ ችግሮች መሆናቸውን  ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል። በህገ ወጥ መንገድ የሚወጣው ሀብትም የቆዳ ኢንዱስትሪና የኤክስፖርት ቄራዎች ፍላጎት አለማሟላቱን ያመለከቱት ዶክተር ገብረ እግዚአብሔር የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ቆዳ ከውጭ ለማስገባት መገደዳቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል። የዘርፉን ልማትና ምርታማነት እድገትን ማፋጠን እንስሳት አርቢው ማህበረሰብ ገበያው የሚፈልገውን ምርት ለማቅረብ  እንደሚያስችለውም ገልጸዋል። የአርሶና አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ፣የፈፃሚዎችን አመለካከት፣ክህሎትና እውቀት በአቅም ግንባታ በማብቃትና ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ለአገልግሎቱ ውጤታማነት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። የዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ተቋም ምርምር እንስቲትዩት ሳይንቲስት ዶክተር ብርሃኑ ገብረመድህን በበኩላቸው የአርሶና አርብቶ አደሩን የእንስሳት አረባብ ሥርዓት ከልማዳዊነት ማውጣትና ገበያ ተኮር እንዲሆን ጥረቱ ማጠናከር ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ በምርቱ አዋጭነትና የገበያ ተወዳዳሪነት ሙያ ድጋፍ ማግኘት እንዳለበት የተናገሩት ዶክተር ብርሃኑ፣ አርሶና አርብቶ አደሩ ህይወቱን የሚለውጥና ትርፍ የሚያገኝበት አሰራርና አረባብ እንዲከተል መታገዝ እንደሚገባው አመልክተዋል። በግብርና ሚኒስቴር የወተት ሀብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ተካ ሚኒስቴሩ  በ150 ወረዳዎች በአንስሳት ሀብት ልማት በተለይም በወተት፣በሥጋ፣ቆዳና ሌጦ፣ዓሣ ሀብት፣ማርና መኖ ልማት ዙሪያ ስልጠና እንደሚሰጥ አስታውቀዋል። በዚህም ገበያ ተኮር የእንስሳት ሀብት ልማት ፓኬጅና ገበያ ተኮር የኤክስቴሽን አገልግሎት ከ12ሺህ በላይ የገጠር ቀበሌዎች ለልማት ጣቢያ ሠራተኞች፣አርሶና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ  ተጠቃሚ እንደሚሆኑበት ተናግረዋል። በስልጠናው ላይ ከ196 በላይ የሚሆኑ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የተወጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም