በስሪላንካ የደረሰው የሽብር ጥቃት ከአለም አቀፍ የሽብርተኛ መረብ ጋር ሊያያዝ ይችላል ተባለ

55
ሚያዝያ 14/2011 ባለፈው እሁድ በስሪላንካ ለ290 ሰዎች ሞትና 500 ሰዎችን ቁስላኛ ያደረገው የሽብር ጥቃት ከአለም አቀፍ የሽብርተኛ መረብ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ተዘገበ። የስሪላንካ መንግስት እምብዛም እውቅና የሌለውን እና በሃገሪቱ የሚንቀሳቀሰውን ናሽናል ቶውሂድ ጃማት የተባለን የሽብር ቡድን ለጥቃቱ ተጠያቂ ቢያደርግም እስካሁን ሃላፊነቱን የወሰደ አካል እንደሌለም በመረጃው ተመልክቷል። ፖሊስም በተከታታይ ቀናት ለተፈፀሙት ጥቃቶች እጃቸው አለበት በሚል 24 ሰዎችን ይዞ ያሰረ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲተወጅም አድርጓል። ሰኞ ዕለት በዋና ከተማዋ ኮሎምቦ በሚገኝ ቤተክርስቲያን አቅራቢያ የፈነዳው ሌላ ፍንዳታም ከተማዋን አናውጧታል፤  ፖሊስ ከመፈንዳቱ በፊት ሊያከሽፈው የነበረ በመኪና ውስጥ ተጠምዶ የነበረ ፈንጂ መፈንዳቱን የጠቀሰው ዘገባው በዚህ ፍንዳታ የደረሰውን የአደጋ መጠን ለማወቅ አለማቻሉንም ጠቁሟል። የሽብር ጥቃቱ ከመፈፀሙ ከሁለት ሳምንታት በፊት ለሃገሪቱ ባለስልጣናት የቦምብ ፍንዳታ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ከናሽናል ቶውሂድ ጃማት አሸባሪ ቡድን ደርሷቸው እንደነበር የስሪላንካ ካቢኔ ቃል አቀባይ ራጂታ ሴናራንቴ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት መናገራቸውን ዘገባው አክሏል። ቃል አቀባዩ አክለውም የቦምብ ጥቃቱን ያደረሱት አካላት ከውጭ ድጋፍ ተደርጎላቸው እንደሆነ ተናግረው በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አሸባሪ ቡድኖች ብቻቸውን መሰል ጥቃቶችን ይፈፅማሉ ብለው እንደማያምኑም አስረድተዋል። አለም አቀፍ የሽብር መረቡን ለመበጣጠስ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በስሪላንካው ፕሬዚዳንት ማይትሪፓላ ሲሪሴና በኩል ጥሪ መደረጉን ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የወጣ ዘገባ ማመልከቱን ቢቢሲ ዘግቧል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም