ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ወጣቶች ላቅ ያለ የቴክኖሎጂ እውቀት እንዲይዙ ማድረግ ይገባል

62
ሚያዝያ 14/20 የጠቅላይ ሚኒስትሩ የከተማና መሰረተ ልማት አማካሪ አቶ ጃንጥራር አባይ የኢንተርፕራይዞችን አቅም ለማሳደግ ከዩኒቨርሲተና ኮሌጆች የሚመረቁ ወጣቶች ላቅ ያለ የቴክኖሎጂ እውቀት እንዲይዙ ማድረግ ያስፈልጋል አሉ። የኢንተርፕራይዞችን አገራዊ አቅም ለማጎልበት ከዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች የሚመረቁ ወጣቶች ላቅ ያለ የቴክኖሎጂ እውቀት ይዘው እንዲወጡ ማድርግ እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የከተማና መሰረተ ልማት አማካሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ። ከሚያዚያ 14 እስከ 19 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄደው ሁለተኛው ዙር አገር አቀፍ የሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ አበባ ተከፍቷል። በዝግጅቱ ላይ ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ195 በላይ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች ተሳትፈዋል። አቶ ጃንጥራር በመክፈቻው ላይ እንዳሉት በሚሊዬን የሚቆጠሩ ዝቅተኛ ገቢ የነበራቸው ዜጎች በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ሃብት ማፍራት ጀምረዋል። ኢንተርፕራይዞቹ የዜጎችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አገራዊው የድህነት ምጣኔ  እንዲቀንስ ማገዙንም ገልጸዋል። በመሆኑም የስራ እድል ፈጠራ መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚፈፅማቸው የልማት አጀንዳዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፉን በማስፋትና ዜጎችን በስራው በማሳተፍ የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ለማፋጠን ይሰራል ብለዋል። የማዕድን ዘርፍ፣ የቤቶች ልማት፣ የስኳር፣ የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን፣ የባቡርና መንገድ ዘርፎች ኢንተርፕራይዞቹ የሚሳተፉባቸው ዋና ዋና ዘርፎች እንደሚሆኑም ጠቁመዋል። ለዚህም ከዩኒቨርሲቲዎችና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶችን በቴክኖሎጂ እውቀታቸው የበለጸጉ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ወጣቶቹ በራሳቸው የሚተማመኑ ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑና የቴክኒክና ሙያ ስራ ፈጠራ ስልጠናዎችን የጥራት ደረጃ ማሻሻልም ቀጣይ ስራ ይሆናል ነው ያሉት። የፌዴራል የከተሞች የሥራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ በዚህ አመት በርካታ ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል። በተያዘው ዓመት በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያለመ  ኤግዚቢሽንና ባዛር ለሁለተኛ ጊዜ መዘጋጀቱንም አስታውሰዋል። በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ8 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች የተሳተፉበት ኤግዚቢሽንና ባዛር መዘጋጀቱን አክለዋል። በዘጠኝ ወራት ብቻ ለኢንተርፕራይዞቹ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ የገበያ ትሰስር መፍጠር ተችሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም