ኢትዮጵያና የኮርያው ኤግዚም ባንክ የ264 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት አደረጉ

48
ኢትዮጵያና የኮርያው ኢምፖርት-ኤክስፖርት (ኤግዚም) ባንክ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚውል የ264 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት አደረጉ። የብድር ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴና የኮሪያው ኤግዚም ባንክ ሲኒየር ኢክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ሚስተር ሺን ዲጎ ዮንግ ናቸው። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የብድር ስምምነቱ በኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህም ለኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ፣ ለመስኖና ለገጠር ልማት ፕሮግራም ይውላል። በዚህም 170 ሚሊዮን ዶላሩ የብድር ስምምነት በደቡባዊ የአገሪቷ ክፍል ለሚደረገው የኤሌክትሪክ መሰመር ዝርጋታ ፕሮጀክት የሚውል ሲሆን ፕሮጀክቱ በሰሜን ምስራቅ የአገሪቷ ክፍልም ተጨማሪ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል። በግንባታ ላይ ላለው ለኦሞ ኩራዝ የስኳር ፍብሪካ ግንባታ፣ ወደፊት ለሚገነባው የአርባምንጭ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ለወጪ ንግድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም በደቡብ ክልል የተመጣጣነና ደረጃውን የጠበቀ ልማት እንዲኖር ለማድረግ እንደሚያግዝም አክለዋል። ሌላው የብድር ስምምነት 94 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰው ይህም ለመስኖና ለገጠር ልማት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ይውላል ሲሉ ገልጸዋል። ይህም ዘላቂ የግብርና ምርት ለመጨመር፣ ዘላቂ የመስኖ መሰረተ ልማት ለመገንባት፣ በኦሮሚያ ክልል በአደኣ በቾ የአርሶ አደሮችን ገቢ በማሳደግ ስር የሰደደ ድህነትን ለማስወገድ ያለመ እንደሆነም ተናግረዋል። የኮሪያው ኤግዚም ባንክ ሲኒየር ኢክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ሚኒስተር ሺ ዲጎ ዮንግ በበኩላቸው በዛሬው እለት የተደረገው የብድር ስምምነት ኢትዮጵያ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ቅድሚያ ለሰጠቻቸው ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ይውላል። በዚህም ስምምነቱ የኃይል መሰረተ ልማት በማሳለጥ ለአገሪቷ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ለማድረግ፣ በደቡብ ክልል አዲስ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባትና በአካበቢው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ያስችላልም ብለዋል። የብድር ስምምነቱ የኮርያ ኤግዚም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከርና ፍላጎት መሰረት አድርጎ የሚሰሩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ለማጎልበት ያግዛል ሲሉም ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም