የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ሽልማት ተበረከተለት

137
ሚያዝያ 14/2011በአፍሪካ ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ሽልማትና የአቀባባል ስነ ስርአት ተደረገለት ፡፡ በኮትዲቭዋር ርዕሰ መዲና አቢጃን በተካሄደው ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ የታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ሆቴል የሽልማትና አቀባባል ስነ ስርአት ተደረገለት። ከሚያዚያ 8 እስከ 12 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያ በ6 ወርቅ፣በ10 ብር፣በ14 የነሐስ፣በድምሩ 30 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አምስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው 39 ሴት እና 43 ወንድ በድምሩ 82 አትሌቶችን በአጭር፣ በመካከለኛ፣ በረጅም ርቀትና በሜዳ ላይ የአትሌቲክስ ስፖርት ተግባራት በሆኑት በውርወራና ዝላይ ስፖርቶች አሳትፋለች። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም ኢትዮጵያ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ  ውድድሮች ከተሳተፎ ባለፈ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት  ህዝቡ የሚጠብቀው ነው ብሏል። በውድድሩ የተገኘው 30 ሜዳሊያ መልካም የሚባል ውጤት የተመዘገበበትና የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ እንዳደረገም ገልጿል። አትሌቲክስ ባህሪው መደጋጋፍን የሚጠይቅ በመሆኑ በውድድሩ የተሳተፉ አትሌቶች ለሜዳሊያው መገኘት ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ምስጋና ይገባቸዋልም ብሏል። በአቢጃኑ ውድድር ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች በወንዶች ስሉዝ ዝላይና ርዝመት ዝላይ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን በሌሎች የሜዳ ተግባራትም ሜዳሊያዎች ውስጥ መግባት የቻለችበትን ውጤት አስመዝግባለች። ቀደም ሲል ኢትዮጵያ እምብዛም በማትታወቅባቸው ውድድሮች ያስመዘገበችው ውጤት አበረታች በመሆኑ ዘላቂነት እንዲኖረው የስፖርቱ ባለሙያዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል ብሏል። ኢትዮጵያ በምትታወቅባቸው የ5 እና 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት አለመቻሏን አስታውሶ በርቀቱ የነበረውን ውጤት ዳግም ለመመለስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እነዲወጡም አሳስቧል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ ቡድን መሪ ፈሪድ መሐመድ የአትሌቲክስ ቡድኑ ለውድድሩ ለ45 ቀናት የተሳካ ዝግጅት ማድረጉን ጠቅሷል። ልኡኩ አቢጃን ከገባ በኋላ ግን የተወሰኑ ችግሮች ገጥመውት እንደነበር ገልጿል። የነበሩት ችግሮች በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉና በአዘጋጁ አካል መፈታታቸውን ጠቅሶ ውድድሩ ፈታኝና ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ነበር ብሏል። በቀጣይ በሚካሄዱት የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች፣የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮናና የቶኪዮ ኦሎምፒክ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቃል ብሏል። ከ20 ዓመት በታች ወንዶች ርዝመት ዝላይ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው አትሌት አዲር ጉር ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ውጤት በማታስመዘግብባቸው ስፖርቶች የተሻለ ውጤት ማግኘቷ የሚያስደስት እንደሆነ ገልጿል። አሁን የተገኘው ውጤት በቀጣይ ውድድሮቹ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራባቸው ልምድ ያገኘበት እንደሆነም ተናግሯል። ከ20 ዓመት በታች ሴቶች የ3 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት አለሚቱ ታሪኩ ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎችን ተቋቁመን ውጤት ይዘን መጥተናል ብላለች። በቀጣይ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ከወዲሁ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ እንደምትጀመርም ጠቁማለች። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ ሆቴል ባለቤት በአጠቃላይ ለአትሌቲክስ ልዑኩ ሽልማት አበርክተዋል። ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ አትሌቶች በቅደም ተከተል ከሶስቱም አካላት በአጠቃላይ የ37 ሺህ ፣ የ21 እና የ10 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፣ የኢትዮጵያ አሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣የኢትዮጵያ ሄቴል ባለቤት  አቶ በላይነህ ክንዴና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች የተዘጋጀውን ሽልማት አበርክተዋል። የአፍሪካ የታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ20 ዓመት በታች ውድድሩ ለ14 ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ከ18 ዓመት በታች ውድድሩ ለ3 ጊዜ ነው የተካሄደው። ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያና ግብጽ ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም