በሀዋሳ የስፖርት ጨዋታዎች እንዳይካሄዱ ምክንያት ሆነዋል የተባሉ 37 ተጠርጣሪዎች ተያዙ

57
ሚያዝያ  14/2011 በሀዋሳ ከተማ  ባለፈው ቅዳሜና እሁድ  ይደረጉ የነበሩ የስፖርት ጨዋታዎች እንዳይካሄዱ ምክንያት ሆነዋል የተባሉ 37  ተጠርጣሪዎች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ። በሀዋሳ ከተማ  ባለፈው ቅዳሜና እሁድ  ይደረጉ የነበሩ የስፖርት ጨዋታዎች እንዳይካሄዱ ምክንያት ሆነዋል የተባሉ 37  ተጠርጣሪዎች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ። የከተማው ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር መስፍን ዴቢሶ እንደተናገሩት ሚያዚያ 12/2011ዓ.ም. ዘጠኝ ሰዓት ላይ  ይጀመር የነበረው የወላይታ ዲቻና የደቡብ ፖሊስ ጨዋታ ከዚህ ቀደም ብሎ የሁለቱ  ቡድኖች ደጋፊዎች በፈጠሩት ግጭት ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ደጋፊዎቹ ተጋጭተው ድንጋይ መወራወር ሲጀምሩ የፀጥታ ኃይሉ ገብቶ የአንደኛውን ክለብ ደጋፊ ከሜዳ በማስወጣት ለማረጋጋት መሞከሩን አመልክተዋል፡፡ ሆኖም ከሜዳ የተጀመረው ሁከት ወደ ከተማው ተዛምቶ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን  ገልጸዋል፡፡ በዚህም 17 ሰዎች መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸው በአዳሬ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ ተደርጎላቸው እንደወጡ ያመለከቱት አዛዡ " አንዲት ወጣት በከፍተኛ ጉዳት በሃዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና ላይ ትገኛለች "ብለዋል፡፡ ፖሊስና ህብረተሰቡ ባደረጉት  የተቀናጀ ጥረት  ሁከቱ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል። የከተማው ፖሊስ አዛዡ እንዳሉት  ሚያዚያ 13/2011ዓ.ም.  በሃዋሳ ከተማና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል ይደረግ የነበረው ጨዋታም የተረጋጋ ሁኔታ ባለመኖሩ ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ፖሊስ ጨዋታዎቹ እንዳይካሄዱ ምክንያት ሆነዋል ያላቸውን 37 ግለሰቦችን በተጠርጣሪነት በቁጥጥር ስር አውሎ  ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ኮማንደር መስፍን አስታውቀዋል፡፡ የሃዋሳ ከተማ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ደስታ ዶጊሶ በበኩላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ  ከፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር ጨዋታዎቹ እንዲሰረዙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ስፖርት ሳይሆን ሌላ ዓላማ ያነገቡ አካላት አቅደው በሰሩት ስራ ጨዋታዎቹ መሰረዛቸውንና ላልተወሰነ ጊዜ መራዘማቸውን አመልክተዋል፡፡ ፖሊስ ችግሩን ፈጥረዋል ብለው ከጠረጠራቸው ግለሰቦች በተጨማሪ ሌሎችንም አጋልጦ ለመስጠት እንዲያስችል በየክፍለ ከተማው ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ "ስፖርት ህዝቦችን የማቀራረብ እንጂ የማለያየት አጀንዳ የለውም " ብለዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም