የኦሮሞና የአማራ ህዝብ አንድነት ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ጥላ ነው—ሽመልስ አብዲሳ

179

ሚያዝያ14/2011 የኦሮሞና የአማራ ህዝብ አንድነት ለሌሎች ኢትትዮጵያዊያን ዜጎች ጥላ እንጂ ስጋት አለመሆኑን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
ከኦሮሚያ ክልል ከየትኛውም አካባቢ የተፈናቀሉ ሁሉንም ዜጎችን ክልሉ ወደመኖሪያ ቀያቸው እንደሚመልስም አረጋግጠዋል።

ትናንት በአምቦ ከተማ በተካሄደው የአማራና የኦሮሞ የህዝብ ለህዝብ ጉባኤ አቶ ሽመልስ አብዲሳና ዶክተር አምባቸው መኮንን ጨምሮ የሁለቱ ህዝቦች ተወካዮችና ከፍተኛ የክልሎቹ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ህዝባዊ ውይይት ተደርጓል።

አቶ ሽመልስ በዚህ ወቅት በታሪክ ህፀፆችን በማንሳት ሁለቱ ህዝብ መካከል መቃቃርና መጠራጠረ እንዲፈጠር መደረጉን አስታውሰው፤ ይሁንና የአማራና ኦሮሞ ህዘብ ግንኙነት ሰፊ መሰረት ስላለው በወሬና በአሉባልታ የሚጠፋ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በአገር ግንባታ ታሪኮቻችንም በአንድ ጉድጓድ የተቀበሩ፣ በአንድ ጽዋ የጠጡ፣ ሉዓላዊነትን በጋራ ያስከበሩ፣ ኢትዮጰያ ቀና ብላ እንድትሄድ ያደረጉ ህዝብ መሆናቸውን አንስተው፤ ይህን ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ዴሞክራሲያዊት፣ ፍትህ የተረጋገጠባት፣ አንድነቷ የማይነቃነቅ አገር ለመፍጠር በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በመስዋትነት የተገነባ የሁለቱ ህዝቦች ታሪካዊ ግንኙነት መጠናከር ኢትዮጵያን ከፍ ያደርጋልም ብለዋል።

የሁለቱ ግንኙነትና አንድነትም ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችን ይዞ የሚቀጥል የተቀደሰ ራዕይና ለሌሎችም ጥላ ከለላ እንጂ ስጋት አይሆንም ነው ያሉት።

ኦሮሞ ከ3 ሺህ ዓመታት በፊት ጀምሮ ያዳበረው አቃፊ ባህል ያለው ታላቅ ሕዝብ እንጂ የማፈናቀል ባህል የለውም ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በክልሉ በየትኛውም አካባቢ የተፈናቀሉ ሁሉንም ዜጎች ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንደሚመልሱም አረጋግጠዋል።

አፈናቃይነት ጠላታችን ነው፤ ማፈናቀልም የሰነፎች፣ የተሸናፊነትና ኋላቀር ተግባር ነው ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንቱ።

የህዝብ ለህዝብ መድረኮችን በሁሉም አቅጣጫ በማስፋትም የኢትዮጵያን አንድነት እንደሚያጠናክሩ በማከል።