ለቅዱስ ያሬድ መታሰቢያ ኃውልት በአክሱም ሊቆም ነው

119
ሚያዝያ14/2011 ሃይማኖታዊ ዜማ፣ ውዝዋዜና አቋቋም ለዓለም ላበረከተው ለቅዱስ ያሬድ በአክሱም ከተማ የመታሰቢያ ኃውልት ሊቆምለት መሆኑን የከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የመታሰቢያ ኃውልቱ የሚቆመው በአክሱም ከተማ ነዋሪ በሆኑ አንድ ባለሃብት በተመደበ በጀት ነው። ከአክሱም ከተማ የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ትላንት ባካሄዱት የምክክር መድረክ በከተማው መሀል ክፍል በተለምዶ ፒያሳ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ኃውልቱ እንዲቆም ከስምምነት ላይ ተደርሷል። የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍጹም በወቅቱ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለሀብቱ ለኃውልቱ ግንባታ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር መድበዋል። በከተማው ኃውልቱን ለማቆም መታሰቡ ተገቢነት አንዳለው የተናገሩት ደግሞ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ መምህር ተክላይ አሰፋ ናቸው። ለኃውልቱ ግንባታ ስኬታማነት ነዋሪው ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አመላክተዋል። በስዕልና ቅርጻቅርጽ የዳበረ ልምድ ያለው ወጣት ዮናስ በላይ በበኩሉ በኃውልቱ ግንባታ ሥራ ላይ የራሱን ድርሻ ለመወጣት ቃል ገብቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም