በአገሪቱ ህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ለማስቀጠል ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ማጠናከር ያስፈልጋል

61
አሶሳ ሚያዝያ 14/ 2011 በአገሪቱ ህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ለማስቀጠል ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ  የኅብረተሰብ ክፍሎች አመለከቱ፡፡ በግልገል በለስ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ሦስተኛው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የባህል ሳምንት ተሳታፊዎች በአገራዊ የጋራ እሴቶች ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂደዋል፡፡ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ወይዘሮ ሙሉነሽ ዋሴ ባቀረቡት የጥናታዊ ጽሁፍ  እንዳመለከቱት ብዝሃነትን እያስተናገደች ያለችውን አገር  አንድነቷን ለማስጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ማጎልበት ወሳኝነት አለው። በአሁኑ ወቅት የአገሪቱን ህልውና የሚፈታተኑና ማንነቷን የማይገልጹ ችግሮች መበራከታቸውን ያወሱት ምሁር፣ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በማጠናከር አገራዊ አንድነትን ለማጎልበት መሥራት እንደሚያስፈልግ  አመልክተዋል። ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ተመስገን ኃይሉ ዜጎችን በማንነት በመከፋፈል ለአገሪቱን አንድነት  ስጋት የሚሆኑ ግጭቶች ለማስቀረት የጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ያሻል ብለዋል፡፡ መጋቢ ዳምጠው አዲስ በበኩላቸው በተለይ ወጣቱ  ትወልድ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን በማጠናከር አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡ አቶ ብዛት አብዬ የተባሉ አስተያየት ሰጪ እንዳስረዱት ባለፈው አንድ ዓመት የተጀመረው አገራዊ ለውጥ የታለመለትን ግብ እንዲመታ አንድነትን ማጠናከር  ያስፈልጋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሠረት በከተማዘዋ እየተካሄደ ያለው የባህል ሳምንት ባህላዊ እሴቶችን ከማሳደግ ባሻገር፤ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ማስጨበጡን ተናግረዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አድጎ አምሳያ በበኩላቸው ሳምንቱ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስተምሮናል ብለዋል፡፡ አገራዊ እሴቶች የሚያሳይ ቲያትር በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቀርቧል፡፡ በከተማዋ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የባህል ሳምንት እስከ ሚያዝያ 21/2011 ድረስ ይቀጥላል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም