ለከተሞች መሰረተ ልማት ማስፋፊያ መርሃ-ግብር ማስፈጸሚያ 860 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል

123
አዲስ አበባ ግንቦት 27/2010 በኢትዮጵያ ለ3ኛ ዙር የከተሞች መሰረተ ልማት ማስፋፊያ መርሃ-ግብር ማስፈፀሚያ 860 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ በጀት መመደቡን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አስታወቀ። በ117 ከተሞች የሚተገበረውና ከስድስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርገው መርሃ-ግብር በመጪው ዓመት ተጀምሮ ለተከታታይ አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ነው። መርሃ-ግብሩ ከዘጠኝ ዓመት በፊት  በ19 ከተሞች መጀመሩን ያስታወሱት በሚኒስቴሩ የከተሞች ገቢ ማሻሻያ ፈንድ ሞቢላይዜሽንና ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አምላኩ አዳሙ መርሃ_ግብሩ በሁለተኛው ዙር ሲተገበር የከተሞቹ ቁጥር ወደ 44 ማደጉን  ተናግረዋል። ለመርሃ-ግብሩ ከተያዘው 860 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ በጀት ውስጥ 249 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋው በኢትዮዽያ መንግስት የተመደበ ሲሆን ቀሪው ከዓለም ባንክና ከፈረንሳይ ልማት ድርጅት የተገኘ እንደሆነ ተገልጿል። በመርሃ-ግብሩ የተካተቱት ከተሞች የተመረጡት የከተማ አስተዳደርና የከተማ ምክር ቤት ያላቸው፣ ማዘጋጃ ቤታዊ መዋቅርን የሚከተሉ  እንዲሁም በከንቲባና በከንቲባ ኮሚቴ  የሚመሩ በሚሉ መመዘኛዎች ነው። በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዙሮች የመርሃ -ግብሩ ትግበራዎች ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ሥራዎች መከናወናቸውን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አቶ ጃንጥራር አባይ ተናግረዋል። የክልል ቴክኒክ ኮሚቴዎችና የሚመለከታቸው ቢሮዎች ቅንጅት አለመኖር  የሙያተኛው በየጊዜው መቀያየር፣ የአካባቢና ማህበራዊ ደህንነት ልየታና ሙስና ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ ችግሮች ተብለው ተጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም