የኢትዮጵያን አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር እንሰራለን-ም/ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ

79

አዲስ አበባ ሚያዚያ 13/2011 የኢትዮጵያን አንድነት ይበልጥ ለማጠናከርና የበለጸገች፣ዲሞክራሲያዊና ፍትህ የሰፈነባት፣ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በጋራ እንሰራለን ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በአምቦ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የኦሮሞና አማራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ ላይ ነው።

"ከአማራ ጋር የከፈልነው መሰዋዕትነት ብዙ ነው" ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ከአማራ ህዝብ ጋር  በአንድ መቃብር ተቀብረናል፣ በአንድነት ሞተን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስጠብቀናል ፤ በመሆኑም የኦሮሞ ህዝብ ከአማራ ህዝብ ጋር ለዘመናት የነበረውን ግንኙነት አጠናክረን ለኢትዮጵያ አንድነት እናውላለን በማለት ተናግረዋል።

አሁንም አንድነታችንን አጠናክረን ይበልጥ የበለጸገች፣ ዲሞክራሲያዊትና ፍትህ የከበረባት፣ አገራዊ ክብሯ ከፍ ያለ፣ እንድነቷ የማይነቃነቅ ኢትዮጵያን ለመፍጠርም በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

የኦሮሞ ህዝብ በባህሉ አቃፊና የአንድነት ዘማሪ መሆኑን ያወሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ  ይህንንም አገራችን ችግር ላይ በወደቀች ጊዜ አባይን ተሻግሮ ወዳጅም ፣ ጠላትም እያየ ከአማራ ህዝብ ጋር መልሶ ተቀላቅለዋል ብለዋል።

"ኦሮሞ  በገዳ ስርዓት የራሱን ልጅ ብቻ ሳይሆን ሌላውን ልጅ እንደራሱ አድርጎ የሚያሳድግ ህዝብ ነው" ይህም የኢትዮጵያዊነታችን ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ኦሮሞ ሌላውን እንደሚገፋ፣ እንደሚያፈናቀልና እራሱን ብቻ እንደሚያስቀድም ተደርጎ፣ በተወሰኑ አካላት የተፈጠሩ የውሸት ንግግሮችና የተሰሩ ትርክቶች የአሮሞን ህዝብ መልካም ስም ለማጥፋት የሚደረግ ነው፤ ነገር ግን የኦሮሞ ህዝብ በባህሉ አቃፊ ነው ሲሉም አጽንተዋል።

በሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ባህርዳር የተዘራው ዘር ኢፍታዊነትንና ጸረ ዲሞክራሲን ፈንግሎ ጥሏል ፤ አሁንም ዛሬ አምቦ ላይ የሚዘራው ዘር ይበልጥ መቀራረብን አንድነትን ፣  ልማትን፣ ብልጽግናን የምናረጋግጥበት ፣ ሰላማችንን የምናስጠብቅበትና ኢትዮጵያን ከፍ የምናደርግበት እና በአንድነት ማማ ላይ የምናቆምበት መሆኑን ላረጋግጣላችሁ እወዳለሁ ሲሉም ተናግረዋል።

"በተለያያ ሴራ፣ በተለያየ ችግር ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎቻችንን በቅርብ ጊዜ ሁሉንም ወደ ቄያቸው  እንመልሳቸዋለን" ሲሉም ቃል ገብተዋል።

አፈናቃይነት ጠላታችን ነው፤ አፈናቃይነት የተሸናፊነት ተግባር ነው፤ አፈናቃይነተ ኋላቀርነት ነው፤ ከ3 ሺህ ዘመን በፊት ማቀፍን ያስለመደው የኦሮሞ ህዝብ ለአፈናቃዮችና ለአፈናቃይነት አስተሳሰብ ቦታ የለውም ሲሉም አስታውሰዋል አቶ ሽመልስ።

የአሮሚያ ክልላዊ መንግትም ይህንን የኦሮሞን ቱባ ባህል በተግባር ላይ በማዋል፣ ከአሁን በኋላ መፈናቀል እንዳይኖር፣ የተፈናቀሉ ወንድሞቻችንም ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ቀን ከሌት እንሰራለንም ብለዋል።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ይበልጥ እናሰፋለን፤ ወደ ምስራቅ ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ እና  ሰሜንም እናሰፋለን፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን እናጠናክራለን ጽንፈኞች ኖሩም አልኖሩም አገራችን አንድነቷን ጠብቃ ትቀጥላለች ሲሉም ጠቁመዋል።

በጽንፈኞች አሉባልታ አንደናገርም ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ መድረኩም በጀግኖች መፍለቂያ በኢትዮጵያኖች መመኪያ ሆና ሁሌም ለኢትዮጵያ ህዝብ መስዋዕትነት በመክፈል በሚታወቀው አምቦ ህዝብ ፊት በመካሄዱም ግንኙነቱን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም