በነጭ ሣርብሔራዊ ፓርክ የተጋረጠው ሰው ሰራሽ አደጋ የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ ውጤት ነው

54

አርባ ምንጭ ሚያዝያ 13/2011 በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ የተጋረጠው ሰው ሰራሽ አደጋ በፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ የመጣ መሆኑን የባህልና ቱርዝም ሚኒስቴር አስታወቀ ።

በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ  የተጋረጠው  ሰው ሰራሽ አደጋ በፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ ውጤት መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በፓርኩ አጠባበቅ ዙሪያ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ንቅናቄ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ቡዘና አልከድር በመድረኩ ላይ የፓርኩ ህልውና አደጋ ላይ የወደቀው በፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ደካማነት ነው ብለዋል።

ህገ-ወጥ ሰፋሪዎችን በአማራጭ ስፍራዎች እንዲሰፍሩ አለማድረግ ለችግሩ መባበስ ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል።

የፓርኩን ድንበር በማስከበር  ረገድ የደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች፣ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ አግባብ ያላቸው ተቀናጅቶ አለመስራት ሌላው ችግር መሆኑን አስረድተዋል።

ፓርኩን የሚያዋስኑ ሦስት ዞኖች በጋራ የተዘጋጀው ዕቅድ ችግሮቹን በዘላቂነት ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን  ምክትል  ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን  ፓርኩ በአገሪቱ ከሰሜን ተራሮች ብሔራዊ  ፓርክ ቀጥሎ በገቢ አቅሙ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ጠቅሰዋል፡፡

ፓርኩ እየገጠሙት ባሉት ችግሮች ሳቢያ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሥነ-ምህዳራዊ ጠቀሜታ  እየቀነሰ መምጣቱን አስረድተዋል።

በፓርኩ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰው ሰራሽ አደጋ ለመቀነስና  የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የምዕራብ ጉጂ፣የሰገንና የጋሞ ዞኖች  የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

አደጋውን ለመቀነስ ዞኖቹ በጋራ የሚያከናውኑት  ዕቅድ እንደሚዘጋጅ  አስታውቀዋል።

ባለ ድርሻ አካላት የፓርኩን ሰው ሰራሽ አደጋዎች በሕግ አግባብ ለመቆጣጠርና የተፋሰስ ልማት በማከናወን የአካባቢውን ስነ-ምህዳሩን በመቀየር ፓርኩን ወደ ቀድሞ ገጽታው ለመመለስ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡

የብሔራዊ ፓርኮችና መጠለያዎች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ገብረመስቀል ግዛውና በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሳይንስ ስነ-ምህዳርተመራማሪ ዶክተር ፋሲል እሸቱ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንዳመለከቱት ፓርኩ በዓመት ከ164 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የማስገኘትና 1ነጥብ 2 ትሪሊዮን የካርቦን ክምችት ዋጋ አለው።

ፓርኩ 91 የአጥቢ፣ 351 የአዕዋፍት፣ 33 የተሳቢ፣ 16 የዓሣ፣ከ700 በላይ ደግሞ የእጽዋት ዝርያዎች ተገልጿል፡፡

ህገ-ወጥ ሰፈራ፣እርሻ፣አደን፣ዓሣ ማጥመድ፣ልቅ ግጦሽ፣ደን ጭፍጨፋና  የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ፓርኩ ዓበይት ተግዳሮቶች መሆናቸዉ ተጠቅሷል።

የሕግ የበላይነት አለመከበር፣የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ያለማከናወን፣የባለ ድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ያለመኖር የፓርኩ ተጨማሪ ችግሮች እንደሆኑም ተነስቷል፡፡

መድረኩላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎችን ጨምሮ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ የሚገኙ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም