ኢትዮጵያ ቡና ባህርዳር ከነማን 5 ለ 0 አሸነፈ

68

ሚያዝያ12/2011  በ21ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና ባህርዳር ከነማን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸነፈ።

በአዲስ አበባ ስቴደየም በተከናወነው በዚሁ ጨዋታ ቡና ፍፁም የበላይነት ወስዶ የተንቀሳቀሰ ሲሆን በ17ኛው ደቂቃ የባህር ዳሩ ተጫዋች አሌክስ አሙዙ በራሱ ጎል ላይ በማስቆጠር ቡናን መሪ አድርጎታል።

ቀሪዎቹን ጎሎች ደግሞ እያሱ ታምሩ በ29ኛው ደቂቃ፣ ሁሴን ሻባኒ በ41ኛውና 88ኛው ደቂቃ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር አቡበክር ናስር በ55ኛው ደቂቃ በማስቆጠሩ ኢትዮጵያ ቡናን አሸናፊ አድርገውታል።

በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበክር ናስርና የባህር ዳሩ ሳለአምላክ ተገኝ እርስ በርስ ግጭት በመፍጠራቸው በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ማሸነፉን ተከትሎ ደረጃውን ከነበረበት 9ኛ ወደ 6ኛ ከፍ ሲያደርግ ባህር ዳር ከነማ ከነበረበት አንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ 7ኛ ላይ ተቀምጧል።

በክልል በተከናወኑ የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ጅማ አባጅፋር ደደቢትን 1 ለ 0፣ ድሬዳዋ ከነማ ወልዋሎ አደግራት ዩኒቨርሲቲን 2 ለ 1 በመርታት ባለ ድል ሆነዋል።

ዛሬ ሊካሄድ የነበረው የደቡብ ፖሊስና ወላይታ ዲቻ ጨዋታ በደጋፊዎች ረብሻ ሳይከናወን ቀርቶ ነገ 3፡00 በሃዋሳ እስታዲየም ሊካሄድ ቀጠሮ መያዙን ሪፖርተራችን ሙሴ መለሰ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም