በአማራ ክልል ሴቶችን በሚፈለገው ልክ ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ እንዳልተቻለ ተጠቆመ

65

 ሚዝያ  12/2011 በአማራ ክልል ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፍ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢታቀድም በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ማድረግ እንዳልተቻለ የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡


በአማራ ክልል ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ  ዘርፍ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢታቀድም በሚፈለገው  ልክ  ተጠቃሚ  ማድረግ እንዳልተቻለ የክልሉ  ሴቶች፣  ህጻናትና  ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማረጋገጥ  ከባለድርሻ  አካላት  ጋር በደሴ  ከተማ መክሯል፡፡

የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ አስናቁ ደረሰ እንደገለጹት ሴቶች በተለያዩ አደረጃጀቶች ተዋቅረው በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ  ዘርፎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታቅዶ ቢሰራም በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፡፡

ለዚህ ደግሞ የአመራሩ የግንዛቤ ጉድለትና ቸልተኝነት፣ የጸጥታ ችግሮች፣  የሴቶች ተስፋ መቁረጥና ማህበራዊ ጫና መብዛት የሚጠቀሱ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አስከዛሬ በነበረው አሰራር ለሰላምና ልማት የተቋቋሙ አደረጃጀቶችን የመንግስት ተላላኪና የፖለቲካ መጠቀሚያ አድርጎ ከማየት ባለፈ የብልሹ  አሰራሮች  መሰግሰጊያና  የግል ጥቅም ማግኛ መንገድ ሆነው እንደነበር በግምገማና በመስክ ምልከታ  መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡

"በቀጣይ መንግስትና አጋር አካላትን በማቀናጀትና እስከ  ቀበሌ ድረስ ውይይቶችን  በማድረግ  ሴቶች በተደራጁበት ፌድሬሽን፣ ነጋዴ ማህበር፣ ሊግ፣ ብድርና ቁጠባ ማህበራትና በተለያዩ አደረጃጀቶቻቸው በተጨባጭ እንዲጠቀሙ እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡

"በተለይ በትምህርት፣ በጤናና በግብርናው  ዘርፍ  እኩል ተጠቃሚ  እንዲሆኑና ጾታዊ  ጥቃቶችና ሌሎች በደሎችንም  መከላከል የሚያስችሉ አደረጃጀቶች ተዘርግተዋል" ብለዋል፡፡

ሴቶችን በተጨባጭ  ተጠቃሚ ለማድረግም በየአካባቢው  የሚደርሰዉን  መፈናቀልና  የሰላም  እጦት ለማስቀረት ሴቶች  ልጆቻቸዉን፣  ባሎቻቸዉንና  ጎረቤቶችን በመምከር የድርሻቸዉን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሃዋ አደም በበኩላቸው የሴቶች ተጠቃሚነት በጅምር ደረጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ጥቃቶች እንዳይደርሱባቸዉ፣ የትምህርት እድል እንዲያገኙ ፣ በጤናዉ ዘርፍም በአቅራቢያቸው ተጠቃሚ  እንዲሆኑና  የእስራ  እድልም ተፈጥሮላቸው የአካባቢያቸውን ሀብት እኩል እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው" ብለዋል

ይሁንና በግንዛቤ ክፍተትና በህግ ጥሰት ምክንያት ሴቶች በሚወራው ልክ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ጠቁመዋል።

በቅርቡ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር በአብዛኛውን  የተጎዱት ሴቶችና ህጻናት  መሆናቸዉን የተናገሩት  ወይዘሮ ሃዋ  "ይህም በመንግስት ድክመትና ፈጣን እርምጃ አለመውሰድ የተፈጠረ ነው" ብለዋል፡፡

"ሴቶች በተደራጁበት የስራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፈንታዬ ጋሻው ናቸዉ፡፡

"ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚደረግው ድጋፍና ክትትል እየተቀዛቀዘ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ያስፈልጋል" ብለዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው መድረክ ከኦሮሞ ብሔረስብ አስተዳደር ዞን፣ ከደሴ ከተማና ከደቡብ ወሎ ዞን ከተውጣጡ አመራሮች በተጨማሪ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሴት አደረጃጀቶችንና አጋር አካለት ወክለው የመጡ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም