አፋን ኦሮሞ ለማሳደግና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍየቋንቋው ምሁራን በጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲያግዙ ተጠየቀ

77

ሚያዝያ 12/2011አፋን ኦሮሞ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ለማሳደግና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የቋንቋው ምሁራን በጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲያግዙ ተጠየቀ 

የመቱ ዩኒቨርስቲ "የኦሮሚኛ ቋንቋ የጥናትና ምርምር ስራ ለሀገሪቱ እድገት ያለው ሚና``"በሚል ሀሳብ ያዘጋጀው የጥናትና ምርምር ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።

ለሁለት ቀናት የተዘጋጀው  ጉባኤው ዛሬ ሲጠናቀቅ  የዩኒቨርስቲው ፕሬዚደንት ዶክተር ተካልኝ ቀጄላ እንደገለጹት  ቋንቋው ከክልል አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለልማትና አንድነት አስተዋጽኦው  እንዲያድግ የቋንቋው ተጠቃሚዎችና ሌሎች ብሄረሰቦች የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።


የቋንቋው መጎልበት የኢትዮጵያን አንድነት ብሎም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖረዉን ትስስር በማጠናከር ረገድ ትልቅ አስተዋጽዎ እንደሚኖረው ተናግረዋል።


የመቱ ዩኒቨርስቲም ካለፈው ዓመት አንስቶ የኦሮሞ  ምርምር ማዕከል በማቋቋም ሳይንሳዊ የሆነ የጥናትና ምርምር ስራ ለማካሄድ እየሰራ መሆኑን  አስታውቀዋል።


ማዕከሉ የኦሮሞ፣ባህል፣ቋንቋና ማንነት በጥልቀትና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማጥናት በሀገር ውስጥና በውጭ በስፋት ለማስተዋወቅ መሆኑን ዶክተር ተካልኝ አስረድተዋል።

አፋን ኦሮሞ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ለማሳደግና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የቋንቋው ምሁራን ለጥናትና ምርምር  ስራዎች ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡

የሰግለን ኢሉ አባገዳ ከሊፋ ሾኖ በበኩላቸው አፋን ኦሮሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የትምህርት ቋንቋ ከሆነ ጀምሮ እየተከናወኑ ያሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ቋንቋውን በማጎልበትና በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።


በቀጣይም ምሁራን ተማሪዎችና የመንግስት አካላት የቋንቋውን ጠቀሜታ ለማሳደግ የተቀናጀ ስራ መስራት እንዳለባቸውም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር አቶ በቀለ ገርባ ባቀረቡት የጥናት ጽሁፍ ላይ  እንዳመለከቱት ቁንቋውን በማጎልበት ረገድ ምሁራን እያደረጉ ካለው ጥረት በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሃን  ተቋማትም ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል።


በቋንቋው የሚሰራጩ የህትመት ሚዲያዎችና የፊልም ስራዎች አሁንም ውስንነት እንዳላቸው ገልጸው በዚህ ዙሪያ የተጠናከረ ስራ  እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

በወሎ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር አቶ ሽመልስ ሀይሉ በበኩላቸው አፋን ኦሮሞ  ከትምህርት እና ከስራ ቋንቋነት ባለፈ የቴክኖሎጂ ቋንቋ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።


``"ቋንቋ እና ሀገረ መንግስት ግንባታ"`` በሚል የጥናት ስራ ማከናውናቸውን ጠቁመው  በዚህም ቀደም ብሎ  በሀገሪቱ የነበረው የአንድ ቋንቋ ፖሊሲ ሌሎች ቋንቋዎችን ከማቀጨጩም ባለፈ በምጣኑ ሀብት ልማትና  ማህበራዊ ትስስር ማበርከት የሚገባቸውን ጠቀሜታ ማስቀረቱን ተናግረዋል።

ዜጎች እርስ በእርስ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከርና የፌዴራል ስርዓቱን ለማጎልበት አንዱ የአንዱን ቋንቋ እንዲረዳ መደረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።


በኦሮሚኛ ቋንቋ ምርምር ጉባኤው  ከሀገሪቱ የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት  የተወጣጡ የቋንቋው ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን  በቋንቋው ዙሪያ ያተኮሩ 15 የምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም