የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን ለማረጋገጥና አደጋን ለመቀነስ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እግዛ አስፈላጊ መሆኑ ተጠቆመ

55

አዳማ ሚያዝያ 12/ 2011 የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን ለማረጋገጥና የተሽከርካሪ አደጋን ለመቀነስ በሚከናወኑ ተግባራት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እግዛ አስፈላጊ መሆኑን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተወያይቷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አስማረ በኢትዮጵያ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የምክር ቤት አባላት ሕብረተሰቡን በማስተማርና ግንዛቤው በማሳደግ በኩል የሚጫወቱት ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ከጊዜ ወደጊዜ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የተሽከርካሪ አደጋ ለመግታትና የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ የምክር ቤቱ እገዛ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ምክር ቤቱ አዋጆችን፣ ደንቦችንና የተለያዩ ህጎችን ከማውጣት ባለፈ በቁጥጥር ሥራው ላይ ጠንካራ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ሕብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤና ትምህርት እንዲያገኝ ከማስቻል አንፃር የህዝብ እንደራሲዎች በተመረጡበት አካባቢ ሲመለሱ በትራፊክ አደጋ እየደረሰ ያለውን ጉዳትና በህጎች ዙሪያ ሕብረተሰቡን በማስተማር እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባም አመልክተዋል።

አቶ ምትኩ እንዳሉት የትራፊክ ደህንነት ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ ከቀጣዩ በጀት ዓመት ጀምሮ ከቅድመ መበደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይሰጣል።

ለእዚህም በአሁኑ ወቅት የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ሥርዓተ ትምህርት በረቂቅ ደረጃ ተቀርጾ በምሁራን የማስተቸትና ግብዓት የማዳበር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

በቀጠቀዩ በጀት ዓመት ከ22 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ጎልማሶች በመንገድ ትራፊክ ደህንነት ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በዕቅድ የተደገፈ የዝግጅት ሥራዎች ከወዲሁ እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የመንገድ ደህንነት ፕሮግራምን በመቅረጽ ከ1 ሺህ በላይ በሚሆኑ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በፕላዝማ ቴሌቭዥን በመታገዝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለተማሪዎች ሲሰጥ መቆየቱንም ገልዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉትችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማትና የብቃት ማረጋገጫ ማዕከላትን ደረጃ ለመስጠት ከኢትዮጵያ ደረጃዎች መዳቢ ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።

"የትራፊክ አደጋውን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን በህዝባዊ ንቅናቄና ተሳትፎ ለማጀብ በሚደረግ ጥረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሚና የጎላ ነው" ብለዋል።

“ባለስልጣኑ በዘርፉ እየተባባሰ የመጣውን ችግር ለመቆጣጠር እያደረገ ላለው እንቅስቃሴ ምቹ የሆኑ ህጎችና ደንቦችን በማውጣትና በማሻሻል ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን” ያሉት ደግሞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዳግሶ ጎና ናቸው።

ህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤና ትምህርት እንዲያገኝ በአዋጆች አተገባበርና ህጎች ተፈፃሚነት ላይ የማስተማር ሥራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የትራንስፖርት ዘርፍ አሰራር ከክልል ክልል ልዩነት እንደሚታይበት ጠቁመው በተለይ ከተሽክርካሪ የወንበር መጠን፣ የመጫን አቅም፣ የታሪፍ መጠን እንዲሁም ከተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት እና ከአሽከርካሪዎች ማስልጠኛ ተቋማት ጋር በተያያዘ ማስተካከያ ለማድረግ በባለስልጣኑ የሚቀርቡ ህጎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ በምክር ቤቱ ጠንካራ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም