መቀሌ አዲስ ምክትል ከንቲባ ተሾመላት

46

ሚያዝያ 12/2011 የመቀሌ ከተማ ምክር ቤት አራተኛ ዘመን 24ኛ መደበኛ ጉባኤ የከተማውን ምክትል ከንቲባ ሹመትና ተጨማሪ መደበኛ በጀትን በማጽደቅ ዛሬ ተጠናቀቀ።

የመቀሌ ከተማ ምክር ቤት አራተኛ ዘመን 24ኛ መደበኛ ጉባኤ የከተማውን ምክትል ከንቲባ ሹመትና ተጨማሪ መደበኛ በጀትን በማጽደቅ ዛሬ ተጠናቀቀ።

ከትናንት ጀምሮ ሲካሄድ የቆየውና ዛሬ ረፋዱ ላይ የተጠናቀቀው ጉባኤ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊትን የከተማው ምክትል ከንቲባ ሆነው እንዲያገለግሉ መርጧቿዋል።

አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት በምክትል ከንቲባነት ከመሾማቸው በፊት በተለያዪ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመስራት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሲሆኑ በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በምክትል ዋና ስራ አስኪያጅነትና በዋና ስራ አስኪያጅነት ያገለገሉ መሆናቸውም ታውቋል።

ምክር ቤቱ በተጨማሪም ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ፣በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ተከስቶ በነበረው ሁከትና ግርግር ምክንያት ለተፈናቀሉ የክልሉ ተወላጆች ድጋፍና ሌሎች መደበኛ ስራዎች ማስፈጸሚያ የሚውል የ19 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር ተጨማሪ በጀት አጽድቋል።

በሚቀጥሉት ጥቂት ወራትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት አጥጋቢ ሆኖው ያልተከናወኑ የወጣቶች የብድር አቅርቦትና የመስሪያና መሸጫ ቦታ የመስጠት ስራ በትኩረት እንደሚከናወን አስታውቋል።

እንዲሁም የወጣቶች የስራ እድል፣ የውሃና የመብራት አቅርቦት፣ የመሬት ካሳ አሰጣጥ ችግሮችና እና የመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ ያለአግባብ መናር ለመፍታት በትኩረት ሊሰሩ ከታቀዱ ስራዎች መካከል እንደሆኑም ምክር ቤቱ አጽንኦት ሰጥቶ ተወያይቶበታል።

በከተማው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ስኬታማ ስራዎች ከታዩባቸው መካከልም የግል ባለሃብቶችን የኢንቨስትመንት ጥያቄ የመመለስ ስራ ቀዳሚው መሆኑን ምክር ቤቱ ተመልክቷል።

በተጠቀሱት ወራት ለ600 ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ለመስጠት አቅዶ 29 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ላስመዘገቡ 749 ባለሃብቶች አዲስ ፍቃድ መስጠቱም ታውቋል።

ባለሃብቶቹ በጨርቃጨርቅ ፣በእንጨት ስራዎች ፣በንግድና እንዱስትሪ፣በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ፣ በወረቀትና ወረቀት ውጤቶች ፣ በመድሃኒት እንዲሁም በኬሚካልና ኬሚካል ውጤቶች እንደሚሰማሩም ነው የተገለጸው።

ከገጠር ወደከተማው በተካለሉ አካባቢዎችም 47 በመቶ ሴቶች ለሚገኙባቸው 9 ሺህ 688 ወጣቶች ቦታ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉ በምክር ቤቱ ተገልጿል።

የወጣቶችን የቦታ ጥያቄ ለማስተናገድ ከ136 ሄክታር መሬት በላይ እንደሚያስፈልግ በተተመለከተው የምክር ቤቱ ጉባኤ ለአንድ ሺህ681 ወጣቶች ቦታ መዘጋጀቱንና ለቀሪዎቹ ደግሞ በ45 ቀናት ውስጥ ለማስተናገድ እቅድ መያዙን አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም