በአዲስ አበባ የተደራጁ የዘረፋ ቡድኖች ስጋት እየፈጠሩ ነው --ነዋሪዎች

106

ሚያዝያ 12/2011 በመዲናዋ የተደራጁ የዘረፋ ቡድኖች ስጋት እየፈጠሩ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ የዘረፋ ቡድኖቹን በቁጥጥር ስር እያዋልኩ ነው ብሏል።

"የተደራጁ የዘረፋ ቡድኖች ስጋት እየፈጠሩብን ነው" ሲሉ ኢዜአ ያጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ "የዘረፋ ቡድኖቹን በቁጥጥር ስር እያዋልኩ ነው" ብሏል።

በአዲስ አበባ ካሉት አስር ክፍለ ከተሞች መካከል የበርካታ አገሮች አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና አለምአቀፍ ተቋማት ሰራተኞች በብዛት መኖሪያቸውን ያደረጉት ቦሌ ክፍለ ከተማ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በ14 ወረዳዎች የተዋቀረው ይህ ክፍለ ከተማ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ባለ ኮከብ ሆቴሎችና ዓለም አቀፍ ተቋማትም መቀመጫ ነው።

በክፍለ ከተማው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተደራጁ የዘረፋ ቡድኖች እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው ነው አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ ነዋሪዎች የገለጹት።

በአሁኑ ጊዜ በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ወንጀል እየተራከተ በመሆኑ ነዋሪዎቹ ከጸጥታ አካላት ጋር ያላቸውን ትብብር በማጠናከር የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የከተማው ነዋሪ የሆነው ያረጋል ሞላ ''የተደራጀ ዝርፊያ እየታየ ነው ለምሳሌ ጠዋት ላይ 11 ሰዓት ተኩል ወጥተሽ ቤተሰብ ልትሸኚ ልትሄጂ ትችይ ይሆናል ግን ተደራጅተው በሚኒባስ የዘረፉበት አጋጣሚ አለ። እንዲሁም መኖሪያ ቤት ዘርፈው በተመሳሳይ ቁልፍ በተለያየ ኬዝ ተጠቅመው ህብረተሰቡን ለስጋት የሚዳርጉ አጋጣሚዎች አሉ'' ብሏል።

''አሁን እኔ በምኖርበት አካባቢ ጥበቃዎችን አጠናክሮ የማደረጀት ሁኔታ እየተካሄደ ነው ምክንያቱም አንዳንድ አካባቢያችን ያሉ ጎረቤቶች ንብረቶች ተዘረፍን በማናውቃቸው ሰዎች ተጠቃን እያሉ ስለሆነ አሁን በምንኖርበት አካባቢ ተደራጅተን   ራሳችንን ለመጠበቅና ለሚመጡትም አደጋዎች ራሳችንን ለመከላከል እየጣርን ነው ፤በመንግስት ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ራሳችንን ተደራጅተን ሁከት የሚፈጥሩ ሰዎችን ለይቶ በማውጣት ወደ ህግ  እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ የራሳችን ግዴታ ነው'' ያሉት የከተማው ነዋሪ  ወይዘሮ ማህሌት ቴሌሙስ   ናቸው።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ነጋሽ እንደሚሉት ኮሚሽኑ በመዲናዋ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።

ይሁንና ወንጀሉን ሙሉ ለሙሉ መከላከል ባለመቻሉ በየጊዜው የሚፈጸሙ ዝርፊያዎችን መኖራቸውን አልካዱም።

በተደራጀ የዘረፋ ወንጀል የተሰማሩ ተጠርጣሪዎች ላይ በጥናት የተመሰረተ ክትተል በማድረግ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ይሁንና በየጊዜው ሌሎች የዘረፋ ቡድኖች እየተፈጠሩ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር ሊተባበር ይገባል ብለዋል።

''የኛንም ሆነ የውጭ አገር ዜጎችን ከወንጀል በመከላከል ደህንነታቸውን የማረጋገጥ ሃላፊነት አለብን ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ተጠርጣሪዎችን ለህግ በማቅረብ እንዲቀጡ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም