የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ በተለያዩ አካባቢዎች የተጀመሩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ

100

ሚያዝያ 12/2011 የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተለያዩ የመንገድ ግንባታዎችን ጎበኙ።

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን የደባርቅ- ዛሪማ (ሊማሊሞ ተለዋጭ) መንገድ፣ በሰሜን ወሎ ዞን የጋሸና- ላሊበላ የመንገድ ግንባታ እንዲሁም በትግራይ ክልል የአዲአቡን- ራማ-መረብ ቋሚ ኮሚቴው የተመለከታቸው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ናቸው።

የደባርቅ- ዛሪማ የዲዛይን ስራና የመንገዱ ግንባታ በቤጂንግ አርባን ኮንስትራክሽን ኩባንያ የተያዘ ሲሆን ግንባታው 68 ነጥብ 621 ኪሎሜትር  ርዝማኔ  አለው፡፡

ለአካባቢው ህብረተሰብ ከፍተኛ የስራ እድል እንደሚፈጥር የሚነገርለት ይህ የመንገድ ፕሮጀከት የኮንትራት ወጪው ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ሲሆን የግንባታው ጊዜ  4 ዓመታትን የሚወስድ  መሆኑ ታውቋል፡፡

ግንባታው በተያዙው ዓመት ጥር ወር ላይ የተጀመረ ሲሆን፤  ታህሳስ 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በምልከታው የመንገድ ፕሮጀክት የዲዛይኑ ለአካባቢው ህብረተሰብ የቅሬታ ምንጭ በማይሆን መልኩ መታየት እንዳለበት አሳስቧል።

 12 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የአዘዞ-ጎንደር የማሻሸያ የመንገድ የግንበታ ሂደትም ቋሚ ኮሚቴው ተመልክቷል።

ከ871 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የተመደበለት የመንገዱ ግንበታ በጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም ተጀምሮ ጥቅምት 2011 ዓ.ም ይጠናቀቃል ቢባልም በተደረገው የዲዛይን ክለሳ መሰረት ነሐሴ 2012 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

በተጨማሪም የጋሸና- ላሊበላ የመንገድ ፕሮጀከት በተያዘለት ጊዜ፣ጥራትና በጀት እንዲጠናቀቅ ከወሰንማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸውም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

ቋሚ ኮሚቴው በአማ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን እየተሰራ ያለውን የጋሸና- ላሊበላ የመንገድ ግንባታም ተመልክቷል።

በመንገዱ ግንባታ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የአከባቢው አስተዳደር አካላት ከግንባታ ተቋራጩ ጋር ተቀራርበው በመስራት ችግሩን እንዲፈቱ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

በቻይና ሬልዌይ ቁጥር 3 ኢንጂነሪንግ የሚሰራው ፕሮጀከት በመጀመሪው የኮንትራክት ውል መሰረት ፕሮጀክቱ የካቲት 2006 ዓ.ም ተጀምሮ ነሐሴ 2009 ዓ.ም መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም እስካሁን አልተጠናቀቀም፡፡

በመንገድ ፕሮጀክቱ ዲዛይን ለአራተኛ ጊዜ ክለሳ ተደርጎበት ጥቅምት 2012 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የመንገዱ ግንባታ በፊት ከነበረው አንፃራዊ በሆነ መልኩ በተሻለ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝም ቋሚ ኮሚቴው ተመልክቷል።

በትግራይ ክልል የአዲ አቡን- ራማ-መረብ የመንገድ ግንባታንም ቋሚ ኮሚቴው ወደ ስፍራው ተጉዞ ተመልክቷል።

በምልክታውም በወሰን ማስከበር ስራ ያሉበትን ችግሮች ፈጥኖ ለመፍታት የአድዋ ከተማ መስተዳደር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተናቦና ተቀናጅቶ እንዲሰራ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴ በመንገዱ ግንባታ ሂደት እና በዋና ዋና ማነቆዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋርም አድርጓል።

የአዲ አቡን- ራማ-መረብ የመንገድ ፕሮጀክት የዲዛይንና የግንባታ ስራው አገርበቀል በሆነው አፍሮፅዮን ኮንስትራክሽን በመከናወን ላይ ይገኛል።

መንገዱ 47 ኪሎሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን የግንባታ ወጪው 807 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ነው።

ጥቅምት 2009 ዓ.ም ተጀምሮ ጥቅምት 2012 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ሲሆን የፕሮጀክቱ አፈፀፀም እስካለፈው መጋቢት ወር ድረስ 27 ነጥብ 83 በመቶ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም