የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዜጎችን መፈናቀል በሚመለከት ጥናት ማካሄዱን አስታወቀ

149

ሚያዝያ 12/2011 ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ጥናቱ የመፈናቀል መንስኤ የሆኑትን ችግሮች በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ያስቀምጣል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት  በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ከሞቀያቸው መፈናቀላቸውን ከመንግስት የወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ይህን ችግር መንግስት ከየሃይማኖት አባቶች፣አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ለመፍታት ጥረት ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ መግለጻቸው አይዘነጋም።

በተለይም የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው የመመለሱንና በተለያዩ አካባቢዎች አስፍሮ እንዲቋቋሙ የመደገፉን ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

አባገዳዎች ከጉጂ ኦሮሚያ የተፈናቀሉ የጌዲዎ ህዝቦችን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በቅርቡ ጥሪ ማቅረባቸውም ይታወሳል።

የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ "ምክር ቤቱ የዜጎች መፈናቀልን በተመለከተ ምን አከናወነ?" በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የተጠናቀቀው ጥናት ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር አቅጣጫ በማስቀመጥ ውጤቱን ይከታተላል።

የጥናቱን ይዘት በዝርዝር ያልገለጹት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ጥናቱ የተካሄደው ዜጎች የተፈናቀሉበት ቦታ ድረስ በማቅናት ሲሆን፤ ትኩረቱም በችግሩ መፍትሄና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ነው።

 ምክር ቤቱ የህግ አስከባሪ ተቋማት ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ በአገሪቷ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።

አስፈጻሚው አካል ጉዳዩን በሚመለከት እየሄደበት ያለው አግባብ መልካም መሆኑን በመጠቆም።

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት በመጡ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መንግስታቸው በዜጎች ለመፈናቀልና ሞት ምክንያት የሆኑ ከአንድ ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን መናገራቸው ይታወሳል።

በሌላ በኩል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የዜጎች መፈናቀል በሚመለከት ጠንካራ አቋም ይዞ እየሰራ አይደለም” የሚል ትችት በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቢሰነዘርም በጥናት ላይ የተመሰረተ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም