ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የእዳ ወጥመድ ሳይሆን ተባባሪ ሀገራትን የጠቀመ ነው - የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ

179

ቤጂንግ ሚያዚያ 12/2011 የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ባለፉት አምስት አመታት ከቻይና ጋር በትብብር የሚሰሩ የማዕቀፉ አባል ሀገራትን በተጨባጭ የጠቀመ እንጂ የእዳ ወጥመድ ወይም የጂኦፖሊቲካል መሳሪያ አለመሆኑን የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ተናገሩ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ቤጂንግ በምታስተናግደው  የቤልት ኤንድ ሮድ ለአለም አቀፍ ትብብር ፎረምን አስመልክተው ለጋዜጠኞች ገለፃ ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

በገለፃቸውም ይህ ኢኒሼቲቭ አንዳንዶች እንደሚሉት የእዳ ወጥመድ ወይም የጂኦፖሊቲካል መሳሪያ ሳይሆን የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የትብብር ስትራቴጂ ነው ብለዋል፡፡

2ኛው የቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም ለአለም አቀፍ ትብብር በመጪው ሀሙስ ይጀመራል፡፡

ለሶስት ቀናት የሚካሄደው ፎረሙ፤ ፈራሚ ሀገራት  ጥራት ያለው ትብብራቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ነው ተብሏል ፡፡

የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንግ ፒንግ በቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር እንደሚያደርጉ እና በተጨማሪ የመሪዎች የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቶችን እንደሚመሩም ተገልጿል።

ማዕቀፉ ባለፉት አምስት አመታት  አባል ሀገራትን የጠቀመ እንጂ የእዳ ወጥመድ  አለመሆኑን የጠቀሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ከቻይና አልፎ ለአለም ከሚያበረክተው ጉልህ አስተዋፅዎ አንፃር ቤልት ኤንድ ሮድ ቻይና የምታስተናግደው ትልቁ ጉባዔ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለ ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሸቲቭ ያለው ግንዛቤ እና አስተያየት  እውነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

ቻይና ባለፉት አምስት አመታት ከቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ተሳታፊ ሀገራት ጋር ያረገችው የንግድ ልውውጥ ከስድስት ትሪሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ከ80 ቢሊዮን ዶላር በላይ በእነዚህ ሀገራት ኢንቨስት ማድረጓን እና  በሀገራቱም ለ300ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ እንደገለጹት በፎረሙ ላይ ከ150 ሀገራት የተውጣጡ ከ5ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እና የ37 ሀገራት መሪዎች ይታደማሉ።

ከ90 በላይ አለም አቀፍ ድርጅቶች፤ የንግዱ ማህበረሰብ እና ሌሎችም እንደሚካፈሉም አረጋግጠዋል።

ከአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ የጅቡቲ፣ ግብፅ፣ ኬንያ፣እና ሞዛብቢክ ሀገራት መሪዎች በ2ኛው የቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም ላይ እንደሚታደሙ ዋንግ ዪ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በ2ኛው የቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም ላይ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብያት ጌታቸው እንደገለጹት ኢትዮጵያ እና ቻይና ባለ ብዙ ዘርፍ ትስስር ያላቸው ሀገራት ናቸው፤ይህ ትስስር በ2ኛው የቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ የሚጠናከርበት ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በአፍሪካ ጠንካራ የቻይና አጋር የሆነችው ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር የተፈራረመችውን የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ስምምነት ለማፅናት ከፍተኛ ፍላጎት  እንዳላት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የቤልት ኤንድ ሮድ ለአለም አቀፍ ትብብር ፎረም ለመጀመሪያ ጊዜ እኤአ ግንቦት 2017 ቻይና ቤጂንግ ከተማ ነበር የተካሄደው፡፡

በወቅቱ በፎረሙ የ29 ሀገራት መሪዎች፤ ከ140 ሀገራት የተውጣጡ 1600 ግለሰቦች እንዲሁም 80 አለም አቀፍ ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡

ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ እኤአ 2013 የተጠነሰሰው በቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንግ ፒንግ ሲሆን ይህም የአለም ሀገራት ህዝቦችን በመሰረተ ልማት እድገት፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ለማስተሳሰር ያለመ ስትራቴጂ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም