በአማራ ክልል ቅርሶች የመፈራረስ አደጋ እየተጋረጠባቸው መሆኑ ተጠቆመ

151

ሚያዝያ 12/2011በአማራ ክልል የሚገኙ ቅርሶች በወቅቱ አስፈላጊ ጥገና ስለማይደረግላቸው የመፈራረስ አደጋ እየተጋረጠባቸው መሆኑን የክልሉ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ፈንድ ጽፈት ቤት አስታወቀ።

የጽፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ የሺሒዋስ ደሳለኝ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ 27 ቅርሶች አስቸኳይ ጥገና ያስፈልጋቸዋል።

ጽፈት ቤቱ ለቅርሶቹ ማስጠገኛ የሚውል ገንዘብ ለማግኘትም በመጪው ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም በደሴ ከተማ የ10 ኪሎ ሜትር ህዝባዊ ሩጫ ለማካሄድ መዘጋጁትን አመልክተዋል።

" ቅርሶቻችን ለመጠገን እንሮጣለን " በሚል መሪ ሃሳብ ለሚካሄደው ሩጫ ከ300 ሺህ በላይ የመሮጫ ቲሸርት መዘጋጀቱን ገልጸው ሕብረተሰቡ ቲሸርት በ60 ብር ገዝቶ በሩጫው ላይ በመሳተፍ አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደኃላፊው ገለጻ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ቅርሶቹ ከክልሉ አልፈው ለአገሪቱ የቱሪዝም መስህብነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

"በአማራ ክልል አስር ብሔራዊ ፓርኮችና በርካታ ሰው ሰራሽ ታሪካዊ ቅርሶች  ይገኛሉ" ያሉት አቶ የሺዋስ ብዙዎቹ ተገቢው እንክብካቤ ስለማይደረግላቸው የአደጋ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

እነዚህን የሀገር ሀብቶች ለመታደግ ህዝቡ በሩጫው ላይ በመሳተፍ የውዴታ ግዴታውን እንዲወጣ አመልክተዋል።

መሰል ሩጫዎችን  በባህር ዳር ከተማና ሌሎች የዞን ከተሞች ላይ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ለሩጫው የሚሆኑ ቲሸርቶችን ስፖንሰር ያደረገው አትሌት መልካሙ ተገኝ በበኩሉ ቅርሶችን ከአደጋ መታደግ ሀገርን ከጥፋት መታደግ መሆኑን ተናግሯል።

"እኔ በግሌ ከ300 ሺህ በላይ ቲሸርት በ60 ብር ዋጋ ድጋፍ ያደረኩት የቅርሶች መውደም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ስለሚያሳስበኝ ነው" ብሏል።

ህዝቡ ለሩጫው የተዘጋጁ ቲሸርቶችን በመግዛት ቅርሶችን ለመጠገን እያጋጠመ ያለውን የገንዘብ እጥረት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጠይቋል ።

ቅርሶችን ለመታደግ በቀጣይ ለሚካሄዱ ህዝባዊ ሩጫዎች ላይ የቲሸርቱን  ዋጋ ለመሸፈን ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጧል።

የፋሲል ግንብና የላል-ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥገና ከሚፈልጉ የክልሉ ታሪካዊ ቅርሶች ይገኟሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም