ለኢንተርፕራይዞች አገራዊ የገበያ ትስሰር ለመፍጠር የሚያስችል አውደ-ርዕይና ባዛር ሊካሄድ ነው

56

አዲስ አበባ ሚያዝያ 11/2011 ለኢንተርፕራይዞች አገራዊ የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል አውድ-ርዕይና ባዛር ሊካሄድ መሆኑን የፌዴራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ዛሬ የባዛሩን መካሄድ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ ወይዘሮ አቦዘነች ነጋሽ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣አውደ-ርዕዩና ባዛሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በአገር አቀፍ ደረጃ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው የሚያችል ነው።

በመሆኑም ኢንተርፕራይዞቹ በመጠን፣በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አገልግሎት አቅርበው በማስተዋወቅና በመሸጥ አትራፊ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል ብለዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በተጋጀው በዚህ አውደ-ርዕይና ባዛር ላይ 185 ሞዴል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚካፋሉ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 50 በመቶ ሴቶችና 3 በመቶ ደግሞ አካል ጉዳተኞች እንደሆኑ ተገልጿል።

ተሳታፊዎቹ የተመለመሉበት አግባብም፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮፕሮሰሲንግ፣ በዕደጥበብ፣ በቴክኖሎጂና ፈጠራ እንዲሁም በምርት ዲዛይን ስራ ላይ የተሰማሩ በስራዎቻቸው ጥራት ሞዴል የሆኑ አምራቾች መሆናቸውም ተገልጿል።

በአውደ-ርዕዩና በባዛሩ ከሚቀርቡ ዋና ዋና ምርቶች መካከል፣ ባህላዊና ዘመናዊ  የጨርቃጨርና አልባሳት ውጤቶች፣ የቆዳ አልባሳትና ምርት፣ ባህላዊ የዕደ-ጥበባትና ቅርጻቅርጽ ውጤቶች፣ የብረታብረት፣የእንጨት ስራና የኢንጅነሪንግ ስራ ውጤቶችና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች እንደሚገኙበትም ተጠቁሟል።

በአውደ-ርዕዩ በኢንተርፕራይዞቹ መካከል ሰፊ የገበያ ትስስርን ከመፍጠር ባሻገርም በተለይ ከክልል ከተሞች ለሚመጡ ተሳታፊዎች የተሞክሮ ልውውጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ያደርጋል ሲሉም ወይዘሮ አቦዘነች አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም