ጃፓን ለሠላም ማስከበር ማዕከል አቅም ግንባታ ፕሮጀክት ድጋፍ አደረገች

55

አዲስ አበባ ሚያዚያ 11/2011 የጃፓን መንግሥት የመከላከያ ሠላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሠላም ማስከበር ተቋም አቅም ግንባታ ፕሮጀክት የሚሆን 729 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረገ።

የድጋፍ ስምምነቱን የፈረሙት የማዕከሉ ተወካይ ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ኃብታሙ ጥላሁን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሃ-ግብር የኢትዮጵያ ኃላፊ ለዊዜ ቻምበርሌን ናቸው።

ድጋፉ በማዕከሉ ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት ከመደገፍ ባሻገር የማስፋፋያ ፕሮጀክቶች ላይ የሚውልነው።

ብርጋዴር ጄኔራል ኃብታሙ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የጃፓን መንግሥት ላለፉት አምስት ዓመታት በሠላም ማስከበር የስልጠና ዘርፍ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

ግጭትን መከላከል፣ የግጭት አስተዳደርና መልሶ ማቋቋም ላይ የተለያዩ የስልጠና መመሪያዎች ዝግጅት ላይ ለአምስት ዙር ድጋፍ እንደተደረገ አብራርተዋል።

በማዕከሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ማገዝ የዚህኛው ድጋፍ ዓላማ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው የመማሪያ ክፍሎችን ማስፋፋት፣ ለምርምርና ጥናት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ማሟላትን ያካተተ ነው።

''ለዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ስራ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቀ ሰላም አስከባሪ ያስፈልጋል'' ያሉት ብርጋዴር ጄኔራል ኃብታሙ ለሰላም ማስከበር የሚሰማሩ አባላት ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና በመውሰድ ብቁ እንዲሆኑ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም