የኪነ-ጥበብ መፍለቂያ ቦታዎችን ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል--- ዶክተር ሂሩት ካሳው

108

ሚያዝያ 11/2011 ሀገር አቀፍ ታዋቂነት ያላቸውን የኪነ-ጥበብ መፍለቂያ ቦታዎችን ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድጋፍ ሊያደረጉ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው አሳሳቡ፡፡

የጎንደር ዩንቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ "የሊቀ መኳስ ኪነ-ጥበብ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ ሃሳቦች"  በሚል ሀሳብ ያዘጋጀው የሁለት ቀናትአውደ ጥናት በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ተካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅት ሚኒስትሯ እንደተናገሩት የሀገሪቱን የኪነጥበብ ሀብቶች ሳይበረዙና ሳይከለሱ ትውልድ ተሻጋሪ ለማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማይተካ ሚና አላቸው፡፡

ኪነ ጥበብ ማህበራዊ መስተጋብሮችንና ባህላዊ እሴቶቻችን የምንገልጽባቸው በመሆኑ በየአካባቢው የሚገኙ የኪነጥበብ መፍለቂያ ቦታዎችን በመጠበቅና በመንከባከብ በኩል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር ዘርፉን ማገዝ አለባቸው፡፡

የጎንደር ዩንቨርሲቲ የአካባቢውን የባህልና የኪነ ጥበብ መፍለቂያ ቦታዎችን በጥናት በመለየት ተረስተውና ሊጠፉ የተቃረቡ  የኪነጥበብ ክዋኔዎችን

ለትውልድ ጠብቆ ለማቆየት የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የበርካታ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች መፍለቂያ በሆነው "ብር ቧክስ" በተባለው ስፍራ የመሰንቆ  ተጫዋቾችን የቆየ ባህል ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ በኩል ዩንቨርሲቲው በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡

ለብር ቧክስ መታሰቢያነት ለሚገነባው ‘’እዝራ የባህል ማእከል’’ አስፈላጊውን የሙያና የበጀት ድጋፍ በማድረግ ውጥኑ እውን እንዲሆን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የበኩሉን ሃላፊነት ይወጣል ብለዋል፡፡

"የተረሱና ሊጠፉ የተቃረቡ የኪነጥበብ ዘርፎች ወደ መድረክ እንዲመጡ በማድረግ ህልውናቸውን ለማስቀጠል ትኩረት  ይደረጋል" ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩንቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ ናቸው፡፡

እዝራ የሚል መጠሪያ የተሰጠውን የብር ቧክስ የባህል ማእከል በሀገር ውስጥም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ዩንቨርሲቲው የእውቀትም ሆነ የሙያ እገዛ ለማድረግ ዩንቨርሲቲው ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዩንቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስና የስነ ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ካሳሁን ተገኘ እንደገለጹት ኮሌጁ የአካባቢውን ባህልና ኪነጥበቡን ለማሳደግ እንዲቻል

የሙዚቃ፣ የቲያትርና የፊልም ትምህርት ክፍሎችን ከፍቶ ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡

ብር ቧክስ ለአሁኑ ዘመን የሙዚቃ ኪነ ጥበብ ማደግ ፈር ቀዳጅና በርካታ ታዋቂ አርቲስቶች የፈለቁበት ስፍራ  መሆኑን ጠቁመው፤ የማሲንቆ ጨዋታን ባህላዊ እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት ኮሌጁ በጥናትና ምርምር ዘርፉን እንደሚግዝ ተናግረዋል፡፡

በብር ቧክስ ቀበሌ ላለፉት 30 አመታት መሰንቆ በመጫወት ረጅም ዘመን ያገለገሉት አቶ ስማቸው አረጋ በበኩላቸው የመሰንቆን ጨዋታ ወጣቱ ትውልድ እንደነውር በመቁጠሩ ሙያው እየተዳከመ መጥቷል፡፡

የጎንደር ዩንቨርሲቲ ለሙያው ክብር በመስጠትና የኪነጥበቡ ህልውና አደጋ ላይ ከመውደቁ በፊት ለመታደግ የጀመራቸው ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡

አውደ ጥናት ዛሬ የተጠናቀቀ ሲሆን በዩንቨርሲቲው  ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ  ውይይት ተካሄዶበታል፤ ከክልል ፣ ከዞንና ከወረዳ የተጋበዙ የባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎችና አመራሮች እንዲሁም የጎንደር ዩንቨርሲቲው ምሁራንና የብር ቧክስ ቀበሌ የማሲንቆ ተጫዋች የኪነጥበብ ባለሙያች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም