የማዕከላዊና የምዕራብ ጎንደር ሕዝብ ባደረገው ድጋፍ የአካባቢው ሰላም እየተመለሰ ነው

85

ጎንደርሚያዝያ 11/2011የማዕከላዊና የምዕራብ ጎንደር ሕዝብ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮው ባደረገው ድጋፍ የአካባቢውን የቀደመ ሰላም በአጭር ጊዜ መመለሱን 31ኛ ክፍለ ጦር አስታወቀ።

ሠራዊቱ ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ለማቋቋም ቤቶችን በመገንባት በጉልበቱና በዕውቀቱ ጭምር ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡

የክፍለ ጦሩ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ደስታ ተመስገን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ክፍለ ጦሩ ወደ አካባቢው ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ ከሠራዊቱ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።

ሠራዊቱ ሕግና ሥርዓት ለማስከበር ያደረገው እንቅስቃሴና ከሕዝቡ ጋር የፈጠረው ሰላማዊ ግንኙነት ተቀባይነቱ እንዲጨምርና ሰላም የማስከበር ተልዕኮውን ለመወጣት እንዳገዘው ተናግረዋል፡፡

የሠራዊቱ አባላት ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች እርቅ እንዲያወርዱ ያደረጉት ጥረት ሰላም ለማስመለስ  ማድረጉን ኮሎኔል ደስታ አመልክተዋል።

"ሕዝቡ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የነበረበት ስጋት ተወግዷል" ያሉት ምክትል አዛዡ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱም ወደ ቀደመ አብሮነቱ መመለስ ጀምሯል ብለዋል።

ከመተማ ጎንደር ተቋርጦና ተቀዛቅዞ የቆየው የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴም በአጭር ጊዜ ወደ ነበረበት እንዲመለስ የሰላሙ መረጋገጥ አመቺ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

ሠራዊቱ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ  እገዛ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሰራዊቱ ሰላም ከማስከበር ተልዕኮው ጎን ለጎን የአካባቢውን ኅብረተሰብ በልማት ሥራዎች በማገዝ ላይ እንደሚገኝ ምክትል አዛዡ አመልክተዋል።

ሠራዊቱ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በጭልጋ ወረዳ ላዛ ቀበሌ በቤት ግንባታ በመሳተፍ  የወገን አለኝታነቱን በተግባር ማረጋገጡን አስታውቀዋል።

በጭልጋ  ወረዳ የላዛ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ሰጤ ማሩ "ወደቀያችን ለተመለስነው ተፈናቃዮች በቤት ግንባታው በመሳተፍ ሠራዊቱ እያደረገ ያለው ድጋፍ ከልብ አስደስቶኛል" ብለዋል።

አርሶ አደር ሲሳይ ካሴ በበኩላቸው "ሠራዊቱ ከግጭቱ ማግስት ጀምሮ ወደ አካባቢያችን በመግባት እኛን መስሎና የህዝቡን ባህል አክብሮ ለአካባቢው ሰላም መስፈን ያደረገው ጥረት ለቀያችን እንድንበቃ አድርጎናል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በጎንደርና አካባቢው በተፈጠረ ግጭት የተፈናቀሉ ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን መልሶ የማቋቋም እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም