በፊልቱ ከተማ የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት መቋረጡ ችግር እንደሆነባቸው ነዋሪዎች ገለጹ

69

ነገሌ- ሚያዚያ 11/2011ዓ.ም በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን የፊልቱ ከተማ የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት  ለአንድ ወር ያህል በመቋረጡ ችግር እንደሆነባቸ በከተማው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ መብራት ኃይል የፊልቱ ከተማ ደንበኞች አገልግሎት በበኩሉ  ችግሩን በአጭር ጊዜ ለማቃለል እየተሰራ ነው ብሏል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል  ወይዘሮ አሚና ሀጂ በከተማው መብራት አንዴ ከተቋረጠ እስኪሰራ  እስከ 20 ቀን መጠበቅ ግዴታናየተለመደ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ባለመኖሩ ጭራሽኑ ችግሩ ቀጥሎ ለአንድ ወር ያህል በመቋረጡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉአመልክተዋል፡፡

መብራት ኃይል ሰራተኞችን ሲጠይቁ  የተቋረጠው እነሱ  ከሚቆጣጠሩት ውጪ  እንደሆነ ከመናገር ባለፈ  ለችግሩ እልባት ሲሰጡ እንደማይታይ በመጥቀስ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዚሁ ከተማ ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ አቶ አህመድ አደም በበኩላቸው" ችግሩ እንዲፈታ ለሱማሌ ክልልና ለደቡብ ሪጂን መብራት ሀይል የደንበኞች አገልግሎት ብናመለክትም ሰሚ አላገኘንም "ብለዋል፡፡

ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጠው የከተማው መጠጥ ውሀ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ በመሆኑ እሱም አብሮ ከተቋረጠአንድ ወር በማለፉ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

የሚመለከተው አካል ለችግሩ መፍትሄ በመስጠት የፊልቱን ከተማ ነዋሪ ህዝብ ከመብራትና ከመጠጥ ውሀ ችግር ማላቀቅእንደሚገባ አመልክተዋል።

የመብራት መቆራረት  ህዝብን ለችግር መንግስትም ለኪሳራ የሚዳርግ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት ደግሞ   የዚሁ ከተማ ነዋሪ ሀጂ ሰይድ አህመድ ናቸው፡፡

የስነ ምግባር ጉድለት የሚታይባቸው የመብራት ኃይል  ሰራተኞች ላይም የእርምትና የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ መብራት ኃይል የፊልቱ ከተማ የደንበኞች አገልግሎት  በበኩሉ በፊልቱ፣ ለብድሬና ቡልቡል ከተሞች ኃይልየሚያከፋፍለው መሳሪያ በመቃጠሉ ችግሩ መፈጠሩን ገልጿል፡፡

በከተማው የደንበኞች አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ዳውድ አብዲ የተቃጠለው " ብሬከር " የተባለው መሳሪያ ተገዝቶ በመተካቱ በቅርብ ቀን ተሰርቶ ችግሩ  እንደሚቃለል ተናግረዋል፡፡

የቀረበው ችግርና ጥያቄ ትክክል ቢሆንም የተቃጠለው መሳሪያ  ተመቻችቶ  የተቋረጠው መስመር እስኪሰራ ጊዜ ስለሚወስድነዋሪው ህዝብ በትእግስት እንዲጠባበቅ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም