ኢትዮጵያ በዓለም የፕሬስ ነፃነት 40 ደረጃዎችን አሻሻለች

53

አዲስ አበባ ሚያዝያ 11/2011 ዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ወይም  ሪፖርተር ዊዝ አውት ቦርደር እኤአ  በ2019 ባወጣው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ደረጃ ኢትዮጵያ 40 ደረጃዎችን በማሻሻል 110ኛ ላይ ተቀምጣለችል።

ዘንድሮ በአፍሪካ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ማዋከብ መቀነሱን ተጠቅሶ አንዳንድ አገራትም ከፍተኛ መሻሻል ማሳየታቸውን በሪፖርቱ አካቷል።

እኤአ በ2018 በመላው አለም 80 ጋዜጠኞች ሲገደሉ ከነዚህ መካከል 49ኙ የተገደሉት በጻፉት ዘገባ ምክንያት  መሆኑን የጠቀሰው መረጃው በተመሳሳይ 60 ጋዜጠኞች ሲታገቱ 348 ጋዜጠኞች ደግሞ ታስረዋል።

ሪፖርቱ በመላው አለም ጋዜጠኞችን የመጥላት ስሜት በእጅጉ ማየሉን ተከትሎ ከፍ ያለ ፍራቻ መኖሩንም ጠቅሷል።

ቀደም ሲል ደህንነታቸው አስተማማኝ ተብለው የነበሩ አገራት ውስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ደህንነት ሁኔታ መቀነስ ማሳየቱንም ሪፖርቱ አመልክቷል።

አምባገነን መንግስታት ባሉባቸው አገሮች ደግሞ በሚዲያው ላይ የሚደረገው ቁጥጥር መጥበቁንም አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የመንግስት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ በአገሪቱ ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞች በጠቅላላ መፈታታቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ አገሪቱ ቀደም ብሎ ከነበረችበት 40 ደረጃዎችን  በማሻሻል 110 ኛ ላይ መቀመጧን አመላክቷል።

ጋምቢያም ከፍተኛ ለውጥ በማሳየት  ወደ 92ኛ  ከፍ ብላለች።ነገር ግን አዲስ መንግስት መመስረቱ ብቻውን ለለውጥ እንደማያግዝ ታንዛኒያን በምሳሌነት አስቀምጧታል።

ታንዛኒያ ከነበረችበት 25ኛ ደረጀ ቁልቁል ወርዳ 118 ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ሞሪታንያም 22 ደረጃዎችን በማሽቆልቆል ወደ 94ኛ ደረጃ ወርዳለች።

በአፍሪካ አሁንም መጥፎ ሁኔታዎች መቀጠላቸውንና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ 154ኛ እንዲሁም ሶማሊያ በጋዜጠኞች ሞት ቀዳሚዋ አገር በመሆን 164ኛ ላይ ትገኛለች።

“በአገራት የሚከናወኑ የፖለቲካ ክርክሮች የእርስ በአርስ ግጭት ወደ መፍጠር አዝማሚያ ማደጋቸውን ተከትሎ ጋዜጠኞችን የመስዋዕት በግ የማድረግ ፍንጮች እየታዩ ሲሆን ዴሞክራሲም ከፍ ያለ አደጋ ላይ ወድቋል” በማለት የድንበር የለሹ ጋዜጠኞች ቡድን ዋና ጸሐፊ ክሪስቶፈር ዲሎር ተናግረዋል።

ኖርዌይ አሁንም ጋዜጠኞች ደህንነታቸው ተጠብቆ በሰላም የሚሰሩባት ቀዳሚ አገር ስትሆን ፊንላንድ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

አምባገነን መንግስታት በመባል የተፈረጁት ቬንዙዋላ 148ኛ፣ ሩሲያ 149ኛ ደረጃን ይዘዋል።

በመስፈሪያው ቬትናም እና ቻይና 176 እና 177ኛ ደረጃን በመያዝ ወደ መጨረሻው አካባቢ ተቀምጠዋል። ኤርትራ በጋዜጠኞች አያያዝ 178 ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ሰሜን ኮሪያ 179ኛ ላይ ትገኛለች።

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ከ180 አገሮች 24 በመቶ የሚሆኑት ጥሩ የሚባለውን ደረጃ ይዘዋል።

ዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሚሰጡትን አፍራሽ አስተያየት ተከትሎ አሜሪካን 48ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል።

ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ የአሜሪካ ጋዜጠኞች ግድያና ዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑም በሪፖርቱ ተጠቅሷል። እኤአ በሰኔ 2018 ሜሪላንድ  በሚገኘው የካፒታል ጋዜጣ ቢሮ ላይ በተከፈተ ተኩስ 4 ጋዜጠኞች መገደላቸውንም ሪፖርቱ አስታውሷል።

በጋዜጠኝነት ስራ ውስጥ ማስፈራራት፣ ስም ማጥፋትና  እና ጥቃት የመሳሰሉት የሙያው ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውም ጠቅሷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም