የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ስያሜውን ወደ "ቱሪዝም ኢትዮጵያ "ሊቀይር ነው

219

አዲስ አበባ ሚያዝያ  11/2011  የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ስያሜውን "ቱሪዝም ኢትዮጵያ" ለመቀየር የሚያስችለውን የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጀ።

የማሻሻያ አዋጁ የቱሪዝም ፈንድ ለማቋቋም የሚያስችልና የተቋሙን ተጠሪነትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያደርግ ነውም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን እንደተናገሩት አዋጁን ለማሻሻል ባለፉት አራት ዓመታት ሲሰራበት ቆይቷል።

በዚህም መሰረት አዲስ የሚቋቋመው ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከስያሜውን ጎን ለጎን ተቋሙ በሚሰራቸው ሥራዎች ማሻሻያ ተደርጓል ነው ያሉት።

ተቋሙ ከዚህ ቀደም በዘርፉ ላይ አሰራርና ሥርዓት ላይ ትኩረት ቢያደርግም በአዲሱ አዋጅ ግን ተቋሙ ዋና ፈጻሚ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በመሆኑም የቱሪዝም መዳረሻ ልማት መሥራት፣ የቱሪስት መስህቦችን ማስተዋወቅና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በራሱ አቅም ያከናውናል ብለዋል።

የቱሪዝም ፈንድ በማቋቋም ወጪዎቹን በራሱ እንዲያሰባስብና ሥራ ላይ እንደሚያውለውም ጠቁመዋል።

ይህም የሚሆነው መንግሥት የተቋሙን ተግባራት ብቻውን ሙሉ በሙሉ ማስፈጸም ስለማይቻል ፈንድ ማሰባሰብ አስፈላጊ በመሆኑ ስለታመነበት ነው ብለዋል። 

ተቋሙም ከዚህ ቀደም አንደነበረው የራሱ ቦርድ እንደሚኖረውና በቦርድ እንደሚተዳደርና ተጠሪነቱ ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆን አስረድተዋል።

በዘርፉ ያሉትን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ የውጭና አገር በቀል ድርጅቶች ሥራቸውን የማቀናጀትና የማስተባባር ሥራም ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።

ረቂቅ አዋጁ ሲሻሻል ከተለያዩ አገራት ልምዶች መቀመራቸውንና ውይይቶች መካሄዳቸውንም ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም