የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለ26 መምህራንና የስራ ኃላፊዎች ማዕረግ ሰጠ

78

ወላይታ ሶዶ ሚያዝያ 11/2011 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለ26 መምህራንና የሰራ ኃላፊዎች የረዳት፣ ተባባሪና የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ መስጠቱን አስታወቀ፡፡

መምህራኑና የስራ ኃላፊዎቹ  በተሰማሩበት ዘርፍ ያበረከቱትን አስተዋፅኦና ያስመዘገቡን ውጤት መሰረት በማድረግ ማዕረጉ የተሰጣቸው መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አሰታውቋል ።

ዩኒቨርሲቲው ብቁ የተማረ የሰዉ ኃይል በማፍራት ተወዳዳሪና ተመራጭ ለመሆን ያለዉን ዕቅድ ለማሳካት በማሰብ ማዕረጉ እንደሰጠ ተመልክቷል።

የዩኒቨርሲቲዉ ኮሙዩኒኬሽንና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ማቴዎስ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ለመምህራኑ 24 የረዳት፣ አንድ የተባባሪና አንድ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ተሰጥቷል፡፡

"የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሚያዝያ 5 ቀን 2011 ዓም ባካሄደው ስብሰባ መሰረት መምህራኑ የተቀመጠውን መስፈርት አሟልተው በመገኘታቸው ማዕረጉ እንዲሰጣቸው ወስኗል"ብለዋል ።

በሴኔቱ  ውሳኔ  መሰረት የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶክተር ታከለ ታደሰ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ  እንደተሰጣቸው ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

በግብርና፣ በጤና፣ በህክምና፣ በትምህርት ጨምሮ በተለያዩ የሙያ መስኮች ዉጤታማና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የምርምር ስራዎችን ማካሄዳቸውና በማህበረሰብ አገልግሎት ተሳትፏቸው  ያስመዘገቡት ስኬት ማዕረጉ እንዲሰጣቸው ካደረጋቸው መስፈርቶች ተጠቃሽ ናቸው ።

እንዲሁም በመማር ማስተማር ሂደትና በተሰማሩበት የኃላፊነትቦታና የአመራሪነት ደረጃ ያሳይዋቸው ትጋት፣ ያስመዘገቡት ዉጤትና ስኬት ማዕረጉን እንዲያገኙ ያስቻሏቸው መስፈርቶች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ታከለ ታደሰ "የተሰጠን ማዕረግ የበለጠ ማህበረተሰቡን የሚጠቅም ስራ እንድንሰራና ኃላፊነታችንን በትጋት እንድንወጣ የሚያነሳሳን ነው" ብለዋል ።

ዩኒቨርሲቲዉ የአሁኑን ጨምሮ ሁለት የሙሉ ፕሮፌሰርነትና ከ70 በላይ የረዳትና ተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ መስጠቱ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም