ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ አጥፊዎችን ማጋለጥ ይገባል…ዶክተር አምባቸው መኮንን

145

ሚያዝያ 10/2011 ለአካባቢው ሰላምና ለህግና ስርዓት መረጋገጥ ህብረተሰቡ ወንጀለኞችን በማጋለጥ ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት የአማራ ክልል ርዕሰ-መስትዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን ገለጹ።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውኃ ከተማ የአማራና የቅማንት ህዝቦች የጋራ እርቅ ውይይት ዛሬ ተደርጓል።

በውይይቱ ወቅት የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንንን እንደተናገሩት ህገ-መንግስታዊ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄን ወደ አልተፈለገ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲገባ ያደረጉ ግለሰቦች ተጠያቂ ይደረጋሉ።

“ወንጀለኞችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ሁለቱም ማህበረሰብ አሁን የተፈጠረን ቂምና ቁርሾ በይቅርታ መፍታት አለበት” ያሉት ዶክተር አምባቸው ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መመለስና እንደገና የማቋቋም ስራ በፍጥነት እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡

“ዜጎችን ደስተኛና በሀገራቸው የሚኮሩ ለማድረግ ህግና ፍትህን ማስከበር ይገባል”በማለት  ህዝቡ የወንጀለኞች መደበቂያ ባለመሆን የህግ የበላይነት እንዲከበርና ፍትህ እንዲሰፍን ሃላፊነት ወስዶ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

አካባቢውን ወደ ነበረበት የልማትና የሰላም ቀጠናነት ለመመለስ የሁለቱ ማህበረሰቦች እርቅ አማራጭ የሌለው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌው በበኩላቸው በጎንደር የነበረው የአንድነትና የሀገር ፍቅር ታሪክን መመለስ እንደሚገባ ገልጸዋል።

“ለልጆቻችን ቂምና በቀልን ማውረስ የለብንም” ያሉ ሲሆን እርቁን ከልባቸው አድርገው ወደ ልማት ስራ መመለስ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ለጥልና እርስ በእርስ ለመገዳደል፣ እንዲሁም ህዝብ በህዝቡ ላይ እንዲነሳ የአካባቢውን ሰላም በማይፈልጉ አካላት የተጠነሰሰውን ሴራ መበጣጠስ እንደሚገባም ገልፀዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን በበኩላቸው እንደገለፁት በሀገር ሽማግሌ የግጭት አፈታት ስርዓት ጥልን በማስወገድ ሰላም ማስፈን ወሳኝ ነገር ለአካባቢው ልማት ወሳኝ ነው።

ዛሬ የተጀመረው የእርቀ ሰላም ኮንፈረንስም አካባቢውን ወደ ነበረበት ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚመልስ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ አመላክተዋል፡፡

ከእርቀ ሰላሙ ተሳታፊዎች መካከል ቄስ አክሊሉ ወርቁ እንደገለፁት ባለፈው በመፀፀት ለወደፊት በአንድነትና በፍቅር ሆኖ ሀገርን ማልማት ተገቢ ነው።

ለዚህም እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም የአካባቢው ህዝብ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

“በአካባቢያችን ሞትና መፈናቀል እንዳይመጣ ሁላችንም የራሳችንን አስተዋፅኦ መወጣት አለብን” ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ገንዘብ ጀምበር ናቸው፡፡

በዚህ ውይይት የክልሉና የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣የሃይማኖት አባቶችና ከዞኑ  ሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች የተገኙ ሲሆን ውይይቱም በእርቅና በይቅርታ ተቋጨቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም